በኩዌት አንዲት ኢትዮጵያዊት ከሰባተኛ ፎቅ ላይ ስትወድቅ የሚያሳይ ቪዲዮ የቀረጸች አሰሪን በቁጥጥር ስር በማዋል ፖሊስ ምርመራ ጀመረ

ኢሳት (መጋቢት 22 ፥ 2009)

የኩዌት ፖሊስ አንዲት ኢትዮጵያዊት ከሰባተኛ ፎቅ ላይ ልትወድቅ ስትል የሚያሳይ ቪዲዮ የቀረጸች አሰሪን በቁጥጥር ስር በማዋል ድርጊቱን በመመርመር ላይ መሆኑን አርብ አስታወቁ።

ኢትዮጵያዊቷ ከፎቁ በመስኮት ከመውደቋ በፊት “ያዙዝ” የሚል የዕርዳታ ጥሪን በተደጋጋሚ ብታሰማም አሰሪዋ ኢትዮጵያዊቷን ከመታደግ ይልቅ ሰብዓዊነት ባልተሞላበት መንገድ ፀያፍ ቃላቶችን ስትጠቀም የሚያሳይ ቪዲዮ በመሰራጨት ላይ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።

ይኸው በተለያዩ የማህበራዊ ድረገጾች በመሰራጨት ላይ ያለውን የቪዲዮ መረጃ ተከትሎ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኩዌት ባለስልጣናት ድርጊቱ በአግባቡ ምርመራ እንዲካሄድበት ዘመቻን ከፍተዋል።

ኢትዮጵያዊቷ አሰሪዋ ልትታደጋት ባለመቻሏ ብትወድቅም በቅርብ ከነበረ ሌላ ባለ አንድ ፎቅ ጣራ ላይ በመውደቅ ህይወቷ መትረፉ ታውቋል።

ይሁንና አደጋው የደረሰባትና ስሟ ይፋ ያልሆነው ኢትዮጵያዊት በእጇ ላይ የመሰበርና ከአንገት በላይ ጉዳት ድርሶባት ወደ ሆስፒታል መወሰዷን የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ተቋማት ዘግበዋል።

በኩዌት ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለችው አሰሪም፣ ቪዲዮውን ስትቀርፅ የነበረው ኢትዮጵያዊቷ ሆን ብላ ራሷን ለማጥፋት ሙከራ እንዳደረገች መረጃ ለመያዝ ነው ስትል ምላሽ ሰጥታለች።

ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና የህግ አካላት አሰሪዋ የሰጠችው ምክንያት እንዲሁም ኢትዮጵያዊቷ እራሷን ለማጥፋት ሞክራለች የተባለው ምላሽ ከእነ ምክንያቱ ምርመራ እንዲካሄድበት አሳስበዋል። የ12 ሰከንድ ቆይታ ያለው ይኸው አሰቃቂ ቪዲዮ፣ በበርካታ ሰዎች በመታየት ላይ ሲሆን ቪዲዮውን የተመለከቱ ግለሰቦችና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የኩዌት ዜጋዋ ባሳየችው ድርጊት በመቆጣት ድርጊቱ ምርመራ እንዲካሄድበት ጥሪን አቅርበዋል።