በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የተገዙ የማምረቻ መሳሪያዎች በኤሌክትሪክ ሃይል ችግር ከአገልግሎት ውጭ እየሆኑ ነው ሲሉ ሚኒስትር አለማየሁ ገለጹ

ታኀሳስ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የውሃ፣ የመስኖና የኢነርጂ ሚኒስትር አለማየሁ ተገኑ ህዳር 26 ቀን 2007፣ በቁጥር ውመአሚ 1/01/67 በጻፉት ደብዳቤ ” በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች በከፍተኛ ወጪ ተገንብተው ለበርካታ ኢንተርፕራይዞች የመስሪያና መሸጫ አገልግሎት የሚውሉ ህንጻዎችና ሼዶች በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት ለታለመላቸው አላማ ለማዋል ” አልተቻለም ብለዋል።

“በእነዚህ ማእከላት ውስጥም በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የገቡና ሊገቡ የተሳቡ የማምረቻ ማሽነሪዎች ምርትን ማምረት አልቻሉም” ያሉት ሚኒስትሩ፣ “በሃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት  ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪው ለሚደረገው ሽግግር ወሳኝ የሆነውን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ወደ ተግባር በማስገባት በሚፈለገው ደረጃ ለማፋጠን አልተቻለም” ሲሉ አክለዋል።

አቶ አለማየሁ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ይደረጋል ቢሉም፣ ችግሩ የሚፈታበትን የጊዜ ገደብ አላስቀመጡም። የሃይል አቅርቦት ችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነም አልጠቀሱም።

በአገር ውስጥ የሚገኙ የግልና የመንግስት የማምረቻ ተቋማት በኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት ስራቸውን ለማከናወን እየተቸገሩ ባለበት ወቅት፣ መንግስት የኤሌክትሪክ ሃይል ለጎረቤት አገሮች በማቅረብ ላይ መሆኑን ይናገራል።