(ኢሳት ዜና– ሐምሌ 18/2009) የመንግስት ባለስልጣናቱንና ነጋዴዎቹን ማሰር የተጀመረው ዛሬ መሆኑን የገለጹት የመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃን እስራቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
ስለታሰሩት ነጋዴዎችም ሆነ ባለስልጣናት ማንነት የተገለጸ ነገር የለም።የመገናኛ ብዙሃኑ ስለታሳሪዎቹ ማንነት ዝርዝር መረጃው እንደደረሳቸው እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ቀን ላይ ይፋ የሆነው የባለስልጣናቱና የነጋዴዎቹ እስራት በመንግስት ባለስልጣናትም ሆነ በሚመለከታቸው የህግ አስፈጻሚ አካላት ይፋዊ መግለጫ ሳይሰጥበት ከቆየ በኋላ ማምሻውን የኮሚኔኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ 34 ሰዎች መታሰራቸውን አስታውቀዋል።የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት 26 ባለስልጣናት እና 7 ነጋዴዎች እንዲሁም አንድ ደላላ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በተመሳሳይ ከ6 ወር በፊት የመንግስት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች ላይ የእስራት ርምጃ መወሰዱን በመንግስት መገናኛ በዙሃን እንዲሁም በፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ ባለስልጣን ጭምር መግለጫ ከተሰጠበት በኋላ ጉዳዩ ለመንፈቅ ያህል ተዳፍኖ ቆይቷል።
በወቅቱ የታሰረ ነጋዴም ሆነ ባለስልጣን እንዳልነበር የሚገልጹ ወገኖች ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ አንደኛው የህወሃት አንጃ እስራቱን በመቃወሙ ታሰረዋል የተባሉት ባላስልጣናትና ነጋዴዎች ወዲያውኑ ተፈተው ጉዳዩ መቋጨቱን የሚገልጹ ወገኖች አሉ።
ታሰሩ የተባሉት ባለስልጣናት ለወራት ማንነታቸው አለመታወቁ እንዲሁም ስለ ፍርድ ሂደቱ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ በህዝብ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
መንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣም ሰዎቹ የት ደረሱ ሲል ከሳምንት በፊት ዘገባ አቅርቧል።
መታሰራቸው እንጂ ማንነታቸውና ጉዳያቸው የት እንደደረሰ የማይታወቀው ግለሰቦች በሚል ርእስ ባቀረበው ዘገባ በተባራሪ ታሰሩ ሲባሉ የሰማናቸው ባለስልጣናት ሹመት ሲጨመርላቸው ታይቷል ሲልም በዘገባው አክሏል።
በወቅቱ በመንግስታዊዎቹና በፓርቲ መገናኛ ብዙሃን በቀረበው ዘገባ ከ130 በላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች መታሰራቸውና እንዲሁም ንብረታቸው መታገዱ ተመልክቷል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ ባለስልጣን ኮማንደር ደስታ አስመላሽ በድምጽና በምስል በሰጡት መግለጫ የታሰሩት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች ንብረቶች መታገዳቸውን ገልጸው ነበር።
በዚህም 8 ትላልቅ የአክሲዮን ድርሻ ፣4 ህንጻ ፣22 መኖሪያ ቤት ፣2 ፋብሪካ፣49 ተሽከርካሪ እንዲሁም ጥሬ ገንዘብ መታገዱን ገልጸው ነበር።
ሆኖም ለወራት ስለታገደው ንብረትም ሆነ ስለታሰሩት ባለስልጣናት ምንም ሳይታውቅ ቆይቶ እንደገና ከወራት በሗላ ባለስልጣናት ታሰሩ የሚለው ዜና መከተሉ በራሱ በመንግስት ደጋፊዎች ዘንድ ጥያቄን አስነስቷል።