ሰኔ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጊምቦ ገዋታና በቦንጋ የተራዘመው ምርጫ ባለፈው ሳምንት ከተጠናቀቀ በሁዋላ፣ የግል ተወዳዳሪው ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የምርጫ ቀስቃሽና አደራጅ የሆነው ምትኩ ወልዴ ፣ ትናንት
ከቀኑ 6 ሰአት ከ 30 ደቂቃ ላይ ፖሊሶች ከቤት አውጥተው የደበደቡት ሲሆን፣ ግለሰቡ በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ቦንጋ ሆስታል ከገባ በሁዋላ፣ ወደ ጅማ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስዷል። ግለሰቡ የደረሰበት ድበደባ ከፍተኛ በመሆኑ
ለህይወቱ አስጊ መሆኑን የዶ/ር አሸብር ደጋፊዎች ተናግረዋል። በዶ/ር አሸብር ቅስቀሳ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉት ሁሉ እየታደኑ በመሆኑ ብዙዎች ከአካባቢው መሸሻቸውን ተናግረዋል።
ዶ/ር አሸብር በፓርላማ በነበራቸው ቆይታ ራሳቸውን የኢህአዴግ ደጋፊ እያደረጉ ሲናገሩ እንደበር ይታወቃል። ከምርጫው በፊት በአንድ ጋዜጣ ላይ ፣ የኢህአዴግ አባል ባይሆኑም ደጋፊ በመሆናቸው ኢህአዴግ የቦንጋን የምክር ቤት ቦታ
ይልቀቅልኝ ብለው በይፋ ተናግረው ነበር።
ኢህአዴግ ያቀረባቸው እጩ አሸንፈዋል በመባላቸው ዶ/ር አሸበር በሚቀጥለው ፓርላማ አይገኙም። የዶ/ር አሸብር የምርጫ ታዛቢዎች የምርጫውን ውጤት አንቀበልም ማለታቸው ተሰምቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜን ጎንደር በአዘዞ ከተማ መምህር ይትባረክ ጌታሁንና መምህር ሲሳይ ፣ አቶ ወርቁ በላይ የተባሉ የቀበሌ ሰራተኛና አቶ ፋንታሁን የሚባሉ የአገር ሽማግሌ ወጣቱን ለትግል እየቀሰቀሳችሁ ነው በሚል 5ኛ ፖሊስ
ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ ያመለክቷል። ግለሰቦቹ የፓርቲ አባል ይሁኑ አይሁኑ ይታወቀ ነገር የለም።