በከተሞች ብቻ 10 ሚሊዮን ራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ታወቀ

መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአገሪቱ የተከሰተው ከፍተኛ ረሃብ 20 ሚሊዮን ያክል በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መዳረጉን የተመለከተ ዘገባ በተደጋጋሚ ቢቀርብም፣ በከተሞች ስላሉ ራሳቸውን መመገብ ስላልቻሉ ነዋሪዎች ግን ብዙም ሲነገር አይሰማም። ይሁን እንጅ ሰሞኑን መንግስት ባመነው በ11 ከተሞች በከፋ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና ራሳቸውን መመገብ የማይችሉ 10 ሚሊዮን ዜጎች መኖራቸውንና እነሱን ለመርዳት 300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ማግኘቱን አስታውቋል።
ብድሩ የተገኘው ከአለም አቀፍ ልማት ማህበር (SDR) ሲሆን፣ በ38 አመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ ነው።
ሰሞኑን ለፖርላማ የቀረበው መግለጫ እንደሚያሳየው በከተሞች አካባቢ በሴፍትኔት ይታቀፋሉ የተባሉ ወገኖች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ራሳቸውን መርዳት የማይችሉ እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የአእምሮ ህመምተኞች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ አረጋዊያን ናቸው።
እስካሁን በመንግስት በኩል 10 ሚሊዮን ሰዎች መራባቸውን፣ 7 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በምግብ ለስራ ታቅፈው የምግብ እርዳታ እየተሰጣቸው መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል። ሰሞኑን ይህ አሃዝ የሚከለስ ሲሆን፣ በምግብ ለስራ የታቀፉትን ሳይጨምር አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉት ሰዎች ቁጥር ከ18 እስከ 20 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል።