የካቲት ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ዘንዘልማ ግቢ ውስጥ በተካሄደው ስልጠና ለመሳተፍ ከአማራ ክልል ከሚገኙ ከተሞች ለመጡ 450 የከተማ ልማት ዘርፍ ባለሙያዎችና ሃላፊዎች በተሰጠው ግምገማ አስር ባለሙያዎች ብቻ የተሰጣቸውን የብቃት መመዘኛ ማለፋቸው የክልሉንና የፌዴራል ሃላፊዎችን ክፉኛ ማስደንገጡን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ባለሙያዎቹና ሃላፊዎች በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የሙያ ሁኔታ የተሰማሩ የከተማ ፕላን ሰራተኞች፣በመሬት ባንክ አገልግሎት የተሰማሩ እና የይዞታ ምዝገባ ኤጀንሲ ላይ በመስራት ላይ የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ስር የተዋቀረው የፌደራል የተቀናጀ ከተማ መሬት መረጃ ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሳቢክ ያሲን በጉዳዩ ላይ ሲናገሩ፣ ከየከተማው የተሰባሰቡት ባለሙያዎች የተሰጠው የደረጃ ሁለት የመግቢያ ፈተና ሲሰጣቸው ብዙም አይቸገሩም በሚል ግምት ይዘው ቢመጡም አራት በመቶ ብቻ ማለፋቸው እንዳስደነገጣቸው ተናግረው በፌደራል ደረጃ የነበራቸው ግምት እያንዳንዱ ሞያተኛ በስራ ላይ ከመቆየቱ የተነሳ ስራውን በሚገባ ያውቀዋል የሚል እምነት ቢይዙም እንደታሰበው አልሆነም ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም ይህ የሚያሳየን አብዛኛው ምሩቃን ከኮሌጅና ዩኒቨርስቲ በመውጣታቸው እና የትምህርቱም አፈጣጠር በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንጂ በክህሎት ላይ ያላተኮረ በመሆኑ አሁን በእጃቸው ይዘው የሚሰሩበትን መሳርያ በአግባቡ ካለማዎቅ የተከሰተ ከፍተኛ የክህሎት ክፍተት እንደነበረባቸው የሚያሳይ መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሙያ ብቃት መመዘኛው ይህ ውጤት ይከሰታል ብለው እንዳላሰቡ የሚናገሩት የአማራ ሙያና ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ተስፋየ የሽዋስ በሰጡት አስተያየት “በተለይ በኮንስትራክሽን ቤቶች ልማት ሚኒስቴር እና በክልሉ የኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ሀላፊነት የሚመራው ከመሬት ይዞታ ጋር የሚያያዘው ይህ ስልጠና፣ ሙያተኞች ቴክኖሎጂን በመጠቀም ስራቸውን የሚያከናውኑበትን ክህሎት የሚጠይቅበት ወቅት በመሆኑ ከነዚህ ጋር በመተዋወቅ እረገድ በርካታ ሙያተኛ ውስንነት አለባቸው” ብለዋል።
የክልሉ የኢንዱስትሪ ከተማ ልማት ቢሮ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ዋና የስራ ሂደት መሪ አብዛኞቹ ባለሙያዎች በደረጃ ሁለት የተማሩትን የተግባር ትምህርት ለመግቢያ ፈተና ሲሰጣቸው መውደቃቸው በዋናነት ከዩኒቨርስቲና ከቴክኒክና ሙያ እንደወጡ ቀጥታ ወደ ስራው ገብተው እየሰሩ ያሉበት ሁኔታ ነበር፡፡ባለሙያዎቹ አሰራራቸው ከልምድ አሰራር ያልተላቀቀ ሰፊ የሆነ የክህሎትና የእውቀት ክፍተት እንዳለው ለመገምገም ተችሎአል ብለዋል፡፡
ከህብረተሰቡ ባገኘነው አስተያየት በአሁኑ ጊዜ ለከፍተኛ ሙስና ተጋልጦ የሚገኘው የመሬትን ጉዳያ በበላይ ሆነው የሚመሩት ባለስልጣናትም ሆኑ ባለሙያዎች ያላቸው የዘርፉ ዕውቀት አሳሳቢ መሆኑ በሙያና ቴክኒክ ኮሌጆች ደረጃ የሚሰጠው ስልጠና በቂ ክህሎትን የማያስጨብጥ እንደሆነ እንደሚያመለክት የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎች፣ የመሬት ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም እና ፍትሃዊ የሆነ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የማይቻልበት ደረጃ መደረሱ አሳዛኝ ክስተት መሆኑንም አክለዋል፡፡