በከባድ የዝናብና የጎርፍ አደጋ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 7 ፥ 2008)
በተለያዩ ክልልች በተያዘው የክረምት ወቅት በሚኖር ከባድ የዝናብና የጎርፍ አደጋ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የብሄራዊ አደጋ ኮሚሽን ማክሰኞ አሳሰበ።
ኮሚሽኑ ባለፈው ወር ወደ 408 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ከቀያቸው ይፈናቀላሉ ሲል ትንበያን ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ቁጥሩ ከ80ሺ በላይ ሊጨምር እንደሚችል አስታውቋል።
በዝናብና በጎርፍ አደጋ ከቀያቸው ይፈናቀላሉ ተብሎ የሚጠበቁ ሰዎችን ለመደገፍ ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ያስታወቀው ኮሚሽኑ ባለፈው ወር በደረሰ ተመሳሳይ አደጋ ከ100 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸውን አስታውሷል።
የአፋር፣ ሶማሊ፣ የደቡብ፣ የአማራ ክልሎች እንዲሁም የሃረሪ ድሬዳዋ ከተማና የአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች በጎርፍና በከባድ ዝናብ ጉዳት ይደርስባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ ስፍራዎች መሆናቸው ታውቋል።
በእነዚሁ ክልሎች የሚጠበቀው የጎርፍ አደጋ የመሬት መንሸራተትን ያስከትላል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን፣ 125 ሺ ሰዎች ለጎርፍ አደጋ እንዳይጋለጡ ታስቦ ወደ ከፍተኛ ቦታዎች እንዲሰፍሩ መደረጉን የብሄራዊ አደጋ ኮሚሽን አመልክቷል።
የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በበኩሉ ጎርፍ በኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ክትትትል እየተደረገ መሆኑን ማክሰኞ ገልጿል።
የሚጥለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ ውሃ ወለድ ተላላፊ በሽታዎችን ጨምሮ ሌሎች የጤና ችግሮችን ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ደግሞ የህክምና ባለሙያዎች አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የተቀሰቀሰውን የአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት በሽታ ተከትሎ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የአለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች አካላት ጥረት እያደረጉ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበሽታው ስርጭት ሁለት ሰዎች ወደህክምና መስጫ ተቋማት መወሰዳቸውን የገለጸ ሲሆን፣ ተጨማሪ ተጠርጣሪ ሰዎች ወደ ተለያዩ የመንግስትና የግል ህክምና መስጫ ተቋማት በመሄድ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
የበሽታው ስርጭት በቶሎ ለመቆጣጠር ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርጉ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።