በኦጋዴን የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀ በመላ ኢትዮጵያ እየደረሰ የሚገኝ ወንጀል ነው ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2008)

በኦጋዴን የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል በመላው ኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያሳይ እንደሆነ ተገለጸ።

በኦጋዴን ህዝብ ላይ በኢህአዴግ ታጣቂዎች የተፈጸመው ወንጀል ተደብቆ የተቀመጠ እና ለመገናኛ ብዙሃን የማይነገር በመሆኑ ተመሳሳይ ወንጀሎች በኦሮሚያ፣ ጋምቤላና፣ አማራ ክልሎች ላይ መፈጸሙን የክሬት ትረስት ፋውንዴሽን ስራ አስኪያጅ ለኢሳት ተናግረዋል። የውጭ መገናኛ ብዙሃን በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመዘገብ ፈቃድ መከልከላቸው ችግሩ ተባብሱ እንዲቀጥል አስተዋጽዖ አድርጓል ተብሏል።

የክሬት ትረስት ፋውንዴሽን ድርጅት ስራ አስኪያጅ የሆኑት ግርሃም ፒብልስ ባለፈው ሳምንት በኦጋዴን ላይ በምስል ተቀናብሮ በቀረበው ዘገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ መንግስት እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጽንዖት ሰጥቶት እንዲመረምረው የሚያግዝ መሆኑን ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስም ፊልሙ ጄኔቫ በሚገኘው በተባበሩት  መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንደታየ ለማወቅ ተችሏል። ፊልሙን ያዩት የምክርቤቱ አባላትም በከፍተኛ የሃዘን ስሜት ተውጠው እንደነበሩ ሚስተር ፒብልስ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በኦጋዴን ሴቶች ላይ በኢትዮጵያ ወታደሮች የተፈጸውን ወንጀል የሚያሳየው ፊልም በአውሮፓ ፓርላማ ለእይታ እንደበቃ ለማወቅ ተችሏል። በእንግሊዝም ከአውሮፓ ህብረት መውጣት ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ሲረጋጉ ለምክር ቤት አባላትና ሰብዓዊ መብት ተቋማት ቀርቦ እንደሚታይ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ስለ ሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ተዓማኒነት የተጠየቁት የክሬት ትረስት ፋውንዴሽን ስራ አስኪያጅ ሲናገሩ፣ “ጭስ ባለበት እሳት አለ” የሚለውን የእንግሊዛውያን አባባል ተጠቅመዋል። በኦጋዴን የታየው የጥቃቱ ሰለባ ሴቶች ምስክርነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በትክክል እንደተፈጸመ ማሳያ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በህጻናት ጭቆና፣ በመሬት ነጠቃና በመገናኛ ብዙሃን ላይ ጥናት ያደረጉ ግርሃም ፒብልስ፣ በኦጋዴን ውስጥ ሲደረግ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በመቃወም አገዛዙን ከድተው በስደት የሚገኙ ወታድሮች ላይ የደረሰውን ሰቆቃ በምስል አቀናብረው ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

መንግስት እየፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቀረት የተጠናከረ ዘመቻና እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግም ፒብልስ ተናግረዋል። አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የእንግሊዝ መንግስት ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ አገራት ቢሆኑም፣ በኢትዮጵያ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በኢትዮጵያውያን ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።

“በኢትዮጵያ ውስጥ ፍርሃት አለ፣ አገሪቷ በዘር፣ በሃይምኖት፣ በክልል ተከፋፍላለች” ያሉት የክሬት ትረስት ፋውንዴሽን ስራ አስኪያጅ፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ህዝቡን በአንድ ላይ በማንቀሳቀስ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት አለባቸው ብለዋል።