በኦጋዴን በ72 ሰዓታት ውስጥ ከ300 በላይ ሰዎች ሞቱ

የካቲት ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምስራቅ ኢትዮጵያ ኦጋዴን ውስጥ በተቀሰቀሰ የኮሌራ ወረሽኝ በ72 ሰዓታት ውስጥ ከ300 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ። የኦጋዴ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር እንዳለው ሰዎቹ እስካሁን የመድሃኒት እና የሕክምና እርዳታ አልተደረገላቸውም።
ወደ አካቢዎቹ የተሰማራ ድንገተኛ አደጋ መከላከያ የሕክምና ቡድን ባለመኖሩም በበሽታው የሚሞቱ ዜጎች ቁጥራቸው ሊጨምር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
በኦጋዴን በሚገኙ በርካታ ከተሞች እና የገጠር መንደሮች ኮሌራው ተባብሶ እየተዛመተ ሲሆን በገጠር አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ሊጠብቁ እንደወጡ እንደሚሞቱ ቤተሰቦቻቸው እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ከሟቾቹ መካከልም በዱር እንስሳት አስከሬናቸው የተበሉ ይገኙበታል። የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የክልሉ ባለስልጣናትም ሆነ ገዥው መንግስት ምንም ዓይነት ጥረት ካለማድረጋቸውም ባሻገር የኮሌራ በሽታው መዛመት እንዳይታወቅ የመሸፋፈን ስራዎችን እየሰሩ ነው።
በኦጋዴን በከፍተኛ ሁኔታ ወረሽኙ የተዛመተባቸው አካባቢዎች ደገሃቡር ጃራ፣ ኒጎብ፤ ቆራሄ ቀብሪዳሃር እና ሸበሌ ሲሆኑ በሽታው በተመሳሳይም በዶሎ፣ አፍዴር እና ሊበንም ተዛምቷል።እንደ ኦብነግ መግለጫ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ብቻ ቁጥራቸው 2 ሽህ በላይ የሚሆኑ የኦጋዴን ነዋሪዎች በኮሌራ በሽታ ሞተዋል።

የኦጋዴን ገጠራማ አካባቢ ነዋሪዎች ከኮሌራ ወረሽኝ በተጨማሪ በረሃብ ተጠቅተዋል። ይህም የነዋሪዎቹን ሕይወት በሰቆቃ እንዲሞላ ያደረገው ሲሆን የአያሌ ዜጎችም ሕይወት እየረገፈ ይገኛል። የመንግስታቱ ድርጅት በበኩሉ በድርቁ ምክንያት በአካባቢው ውሃ የቀላቀለ የተቅማጥ በሽታ እና ኮሌራ ወረሽኝ መዛመቱን ገልጿል። በቀላል መድሃኒቶች የዜጎችን ሕይወት ማትረፍ እየተቻለ ምንም ዓይነት መድሃኒት ሳይሰጣቸው እንዲሞቱ ተደርገዋል የሚለው ኦብነግ፤ወደ ጎረቤት አገራት በመሄድ መድሃኒቶችን እንዳያገኙም ሁሉ ነገር ዝግ ተደርጎባቸው ባለቡት ስፍራ ሕይወታቸውን እያጡ ነው ብሏል።
የኦጋዴን ሕዝብ ሕክምና የማግኘት መብቱን ተነፍጎ በኢትዮጵያ መንግስት እንዲሞት እየተደረገ ነው በማለትም ለዓለም የጤና ድርጅት የኦጋዴን ነጻነት ግንባር ሪፖርት አድርጓል። ግንባሩ በዚሁ ሪፖርቱ ገዥው ፓርቲ ለሚፈጽማቸው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ ነው ብሏል።
የአፍሪካ ኅብረት፣ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የአሜሪካ መንግስትና ሌሎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አፋጣኝ እርዳታ በማድረግ የዜጎችን ሕይወት እንዲታደጉ ሲልም ኦብነግ ጥሪውን አቅርቧል