ሐምሌ ፭ ( አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ የተካሄደውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ከኦነግ ጋር በተያያዘ በሽብር ወንጀል ተከሰው በታሰሩ 22 ተከሳሾች ላይ አቃቢ ህግ ምስክሮቹ በዝግ ችሎት እንዲታዩለት ጥያቄ አቅርቧል። ከተከሳሾች መካከል በአንደኛ ቁጥር ላይ የሚገኘው ደረጀ አለሙ ከእስር ቤት በማምለጡ ጉዳዩ በሌለበት በመታየት ላይ ነው።
አቃቢ ህግ ሀምሌ 3 ቀን 2009 ዓም ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በጻፈው ደብዳቤ፣ “በ1ኛ እና 2ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀሱትን የአቃቢ ህግ ምስክሮች አቅርበን ለማሰማት ጉዳዩ በመደበኛ የችሎት አሰማም ሂደት የሚካሄድ ከሆነ ምስክሮች በታዳሚ ወይንም በተከሳሾች ቤተሰቦች በአካል መታወቅና መለየታቸው፣ በራሳቸውም ሆነ በቤተሰቦቻቸው ላይ ጥፋት ሊፈጸም የሚችል መሆኑን ጠቅሷል። በተጨባጭም ይህ ፍርሃት ያለባቸው መሆኑንና ዛቻም እየረደሰባቸው መሆኑን የገለጹንልን በመሆኑ እንዲሁም 1ኛ ፣ 10ኛ፣ እና 11ኛ ተከሳሾች አሁንም በቁጥጥር ስር ስላልዋሉና ሌሎችም በወንጀሉ በዋናነት ተካፋይ የነበሩ ተጠርጣሪዎች አሁንም ድረስ በክትትል ስር ስለሚገኙ፣ ፍርድ ቤቱ ሁለቱን ምስክሮች በዝግ ችሎት” ይስማልኝ ብሎአል።
ጉዳዩን የሚከታተሉት ሰዎች በበኩላቸው በምስክርነት የሚቀርቡት ሁለቱ ሰዎች ማንነታቸው እንዳይታወቅ የተፈለገው የደህንነት አባላት ስለሆኑ ነው ይላሉ።
ከተከሳሾች መካከል አንደኛው ተከሳሽ ደረጃ አለሙ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እስር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በማምለጡ ክሱ በሌለበት እየታየ ነው። ደረጀን አስመልጧል የተባለው ዳዊት የተባለው ፖሊስም፣ 6 እስረኞችን ይዞ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እስር ቤት አምልጧል። ማእከላዊ እስር ቤት ማሰሪያ ቦታዎች ሲሞሉበት እስረኞችን በአደራ መልክ ለአዲስ አበባ ፖሊስ የሚሰጥ ሲሆን፣ እስረኞች ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ እንደተዛወሩ ጠፍተዋል።
በዚሁ መዝገብ የተከሰሱት አቶ ዋቅቶላ ፉፋ እና አቶ መልካሙ ወልተጀን ጨምሮ ብዙዎቹ ባለሃብቶች ናቸው። ቡልቲ ተሰማ የሚባለው ተከሳሽ ደግሞ የሰመጉ ሰራተኛ ነበር።