በኦሮምያ የክልል ከተሞች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የኦሮምያ ክልል መንግስት አስታወቀ

ኢሳት (ሃምሌ 19 ፥ 2008)

በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ዳግም ተቀስቅሶ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ማክሰኞ አስታወቀ።

ዳግም ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መግለጫን ያወጣው የኦሮሚያ ክልል መንግስት በምዕራብ አርሲ ዞን እና በምስራቅ ሃረርጌ ጉራዋ ወረዳ እየተካሄዱ ባሉ ተቃዋሚዎች የአንዲት ሴት ህይወት ማለፉንና አምስት ሰዎች መጎዳታቸውን ገልጿል።

በምዕራብ አርሲ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች በመካሄድ ላይ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ ነዋሪዎች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች እንዲፈቱና በክልሉ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን እማኞች ሰኞ ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።

በዶዶላ፣ አዳባና አሳሳ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሃይል እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ነዋሪዎች አስረድተዋል።

ለወራት በኦሮሚያ ክልል ከዘለቀው ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥያቄን እያቀረቡ ያሉ ነዋሪዎች መንገድ በመዝጋት ተቃውሞ እያሰሙ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ይሁንና፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት የጥፋት ሃይሎች ሲል የገለጻቸው አካላት “በህዝብ ዘንድ ይሁንታና ፈቃድ የተመሰረተን መንግስት እንጥላለን” በማለት እንቅስቃሴን እያካሄዱ ነው በማለት ምላሽን ሰጥቷል።

በምስራቅ ሃረርጌ በተመሳሳይ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ባሉ ተቃውሞዎች የአንዲት ሴት ህይወት ማለፉን ያስታወቀው የክልሉ መንግስት በአርሲ ዞን ስለደረሰው ጉዳት የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው በስፍራው አለመረጋጋት በመስፈኑ በነዋሪዎች ላይ የደረሰን ጉዳት በአግባቡ ማወቅ እንዳልተቻለ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።

በምዕራብ አርሲ በዶዶላ አካባቢ ስምንት የወረዳው የተለያዩ ጽ/ቤቶች በእሳት መውደማቸውን የክልሉ መንግስት የገለጸ ሲሆን፣ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለህግ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አክሎ አመልክቷል።

በቅርቡ በምስራቅ ሃረርጌ እና በምዕራብ አርሲ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎችና ከተሞች ዳግም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ማክሰኞ መቀጠሉንና በርካታ የጸጥታ ሃይሎች ወደ አካባቢው በመጓዝ ላይ መሆናቸው ታውቋል።