ታኀሳስ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ ላለፉት 2 ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ዛሬም መቀጠሉን ከተለያዩ አካባቢዎች የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ገዢው ፓርቲ ተቃውሞውን ለመከላከል መከላከያ ሰራዊቱን ሳይቀር አሰማርቶ በወሰደው እርምጃ ከ45 ሰዎች በላይ ተገድለዋል፤ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል። በመላ ኦሮምያ በሚገኙ ከተሞች የፀጥታ ሃይሎች እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ጥረት ያደርጋሉ።የመንግስት ባለስልጣናት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተግባራዊ አይደረግም በማለት ህዝቡን ለማሳመን ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካለቸውም። በየቀኑ እየጨመረ የመጣው ተቃውሞ ያሳሳበው መንግስት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ሲሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ክስ እያቀረቡ ነው። ከወሊሶ 100 ኪሜትር ርቅት ላይ በምትገኘው አመያ ወረዳ ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ከአካባቢው እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን፣ የገዢው ፓርቲ አባላት ነዋሪዎች እርስ በርስ እንዲጋጩ ሲቀሰቅሱ መሰንበታቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ንቅናቄ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ በቀለ ነገአ በአመያ ድርጊቱን በጽኑ ኮንነዋል። ገዢው ፓርቲ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል። ህዝቡም በመንግስት ቅስቀሳ እንዳይታለል መክረዋል ዛሬ ተቃውሞ የተካሄደው በኢሊባቦር ጨዋካ አካባቢ፣ በአርሲ ዶዶላ፣ በምእራብ ሸዋ ግንደበረት፣ ጀልዱ፣ በምእራብ ወለጋ ጊዳኒ፣ አምቦ፣ ቡራዩ፣ ደምቢዶሎ እና ቆቃ አካባቢዎች ናቸው። በቆቃ በተካሄደው ተቃውሞ ገመዳ ገመቹ እና ግርማ ቶሎሳ የሚባሉ የከተማው ነዋሪዎች ተገድለዋል። ከተማው በሙሉ በፌደራል ፖሊስ ተከቧል።
በቡራዩ የተካሄደው ተቃውሞ ከባድ እንደነበር የሚገልጹት የአይን እማኞች፣ የመንግስት ታጣቂዎች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ሰዎች ተጎድተው ወደ ተለያዩ የህክምና ተቋማት ተወስደዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በምእራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ የፌደራል ፖሊስ አባላት በህዝቡ ላይ እርምጃ ሲወስዱ ፣ አድማ በታኝ ፖሊሶች በመቃወማቸው እርስ በርስ የተጣሉ ሲሆን፣ 4 የአድማ በታኝ ፖሊሶች ተጎድተዋል። ይህንኑ ግጭት ተከትሎ ይሁን አይሁን ባይታወቅም፣ የኦሮምያ አካባቢ አስተዳደር ጸጥታ የማስከበሩን ስራ በፌደራል መንግስቱ ተነጥቋል። በሃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው ዋና ማዘዣ የመከላከያ ዋና ኢታማጆር ሹሙን፣ የፌደራል ፖሊስ አዛዡን፣ የደህንነት ሃላፊውንና የክልሉን መሪ ያቀፈ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰማያዊ ፓርቲ ለተገደሉት እና ጉዳት ለደረሰባቸው አጋርነቱን ገልጿል። ከመድረክ እና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመስራት መወሰኑምን አስታውቋል። ፓርቲው ታህሳስ 3/2008 ዓ.ም በካሄደው የብሄራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ከ‹‹ማስተር ፕላኑ›› ጋር በተያያዘ ለተገደሉትና ጉዳት ለደረሰባቸው የህሊና ፀሎት ያደረገ ሲሆን አጋርነቱን መግለፁንም የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
የፓርቲው ብሄራዊ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ውይይት ያደረገ ሲሆን የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በተቃወሙት ኢትዮጵያውያን ላይ መንግስት እየወሰደ ያለው ኢ-ሰብአዊ እርምጃ እና ለሱዳን በሚሰጠው መሬት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
ፓርቲ ከመድረክ ጋር ለመስራት ውይይት መጀመሩን የገለፁት አቶ ይድነቃቸው ከበደ በቀጣይም ከመድረክና ከሌሎች በወቅታዊ ችግሮች ላይ ለመስራት ፈቃደኛ ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር እንዲሰራ ብሄራዊ ምክር ቤቱ ወስኗል።