ኀዳር ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት፣ የኦሮምያ ክልል ልዩ ሃይል እና የፌደራሉ አድማ ብተና ተቃውሞውን ለመቆጣጠር ባለመቻላቸውና የተቃውሞው አድማስ እየሰፋ በመሄዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የፌደራል ዩኒፎርም ለብሰው ተቀላልቅለዋል።
ለሳምንት የዘለቀው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እንዲሁም ከጉደር ወደ ወለጋ የሚወስዱት መንገዶች በመዘጋታቸው የትራንስፖርት አግልግሎት ለሰአታት ተቋርጧል። መልከ ጡሪ አካባቢ በነበረው ተቃውሞ መኪኖች የተሰባበሩ ሲሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፌደራልና የመከላከያ አባላት ወደ አካባቢው በመሄድ ተቃውሞን ቢበትኑትም፣ ውጥረቱ ግን አሁንም እንዳለ ነው።
በጀልዱ እና ጋሊሳ ከተሞች አርሶ አደሩና ተማሪው በጋራ በመሆን ባስነሱት ተቃውሞ በእለቱ መዋል የነበረበት ገበያ ፈርሷል። አርሶ አደሮች እርምጃ ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን የክልሉ ልዩ ሃይል አባላትን በዱላና በነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ለመቋቋም ሲሰባሰቡ፣ ፖሊሶቹ አካባቢውን ጥለው የተመሰሉ ሲሆን፣ ወዲያውኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ ስፍራው ሄደው ሰልፈኛውን ለመበተን ሙከራ አድርገዋል።
በሽጉጤ ከተማ ደግሞ ከቀብር የተመለሱ ወጣቶች መንገዱን በድንጋይ በመዝጋት ፈጥኖ ደራሾች እንዳይንቀሳቀሱ ያደረጉ ሲሆን፣ የባለስልጣናትንና የካድሬዎችን ቤቶች በድንጋይ ደብድበው ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። ተቃውሞው ከፖሊስ አቅም በላይ በመሆኑ ፌደራሎችና መከላከያዎች ወደ አካባቢው ተሰማርተዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ ታጣቂ ፖሊሶች ወደ ውስጥ በመግባት በርካታ ተማሪዎችን ደብደብዋል። በርካታ ተማሪዎች ከድብደባው ለመሸሽ ከግቢ ወጥተው በየዛፍ ስር አድረዋል፡፡ የልዩ ሃይል ታጣቂዎችና ፖሊሶች በተማሪዎች ላይ እየወሰዱት ያለው እርምጃ ዘግናኝ ነው ሲሉ የአይን እማኞች ተናግረዋል። ተማሪዎች ከከተማው እንዳይወጡና የሚኒባስ አሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይሰጡዋቸው ታዘዋል።
በአርሲ ነገሌም እንዲሁ ተመሳሳይ አመጽ ተነስቷል። በጉጂ ዞን በቦሬ ወረዳ የቦሬ 2ኛ ደረጃ ፣ የቦሬ 1ኛ፣ የቦሬ መሰናዶ ተማሪዎች ተቃውሞ ሲያካሂዱ አርፍደዋል። የአዳማና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በኦሮምያና በጎንደር የተገደሉ ዜጎችን በማስታወስ ምግብ ባለመመገብ እና ጥቁር ልብስ በመልበስ ተቃውአቸውን ገልጸዋል።
ጥያቄው የመብት፣ የነጻነት፣ የእኩልነትና የዲሞክራሲ እየሆነ መምጣቱን ከሚሰሙት መፈክሮች ለመረዳት ይቻላል በማለት የአይን እማኞች ተናግረዋል።
ማንኛውም ተማሪ ከከተማ እንዳይወጣ ተከልክሉአል ለሚንባስ ሹፌሮችም ማስጠንቀቂያ ተሰቷቸዋል አንድም ተማሪ እንዳትጭኑ ተብለዋል ተማሪወችም መሞት አንፈልግም ቤተሰብ እየተጨነቀ ነው እንሄዳለን ቢሉም ከኬላላይና ከመነአሪያ እየመለሱአቸው ነው በግድ ወደ ዶር ተመለሱ ተብለዋል የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ሊግ ባወጣው መግለጫ ባለፉት 7 ቀናት ብቻ 9 ተማሪዎች ተገድለዋል ብሎአል። የሰብአዊ መብት ሊጉ የማቾችን ስም ሲዘረዝር ገዛሃኝ ኦሊቃ የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪና የሆድሮጉድሩ ተወላጅ፣ ጉቱ አበራ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪና የጉሊሶ ተወላጅ፣ ካርሳ ቻላ የጉሊሶ ነዋሪ፣ ደበላ ጣፋ ሮቢ የፍቼ ነዋሪ ደጀኔ ሰርቤሳ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪና የቶሌ ተወላጅ፣ ሚፍታህ ጁነዲ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እና የፋርዳ ነዋሪ፣ ሙራታ አብዲ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪና የሀሮማያ ተወላጅ፣ በቀለ ሳቦቃ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪና የአዳ በርጋ ነዋሪ እንዲሁም ኢቤሳ ቡቾ የሆድሮጉድሩ ነዋሪ ብሎአል።
ከፊንጫ ዘሪሁን ረጋሳ፣ ዋቅጅራ ጋዲሳ ፣ መሰረት ጥላሁንና አለሙ ሊቂሳ ሆስፒታል ተወስደዋል። ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል እየታከሙ ነው። ህጻናት እና ወጣቶች የጥይት እራት መሆናቸውን ድርጅቱ ኮንኗል። በዶ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው ኦፌኮ ባወጣው መግለጫ ደግሞ የሟቾችን ቁጥር 10 አድርሶታል። 150 ተማሪዎች መቁሰላቸውን፣ ከ500 በላይ ተማሪዎች መታሰራቸውን እንዲሁም በክልሉ በአብዛኛው ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ድርጅቱ ገልጿል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ መንግስት ራሱ በጀመረውና ባቀጣጠለው ህገወጥ ስራ የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንዲፈታ፣ በኦሮሞ ወጣቶችና ህዝብ ላይ የሚካሄደው ወከባ ፣ ድብደባ፣ እስራትና ግድያ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ለተገደሉትም ለቤተሰቦቻቸውም ተገቢው ካሳ እንዲከፈል፣ ወንጀል የሰሩትም ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲሁም አዲሱ የተቀናጀ ማስተር ፕላን በተገቢው የመንግስት አካል እንዲሻርና የአዲስ አበባና የኦሮምያ ድንበር ወደ ቀድሞው እንዲመለስ ጠይቋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኖርዌይ ኤምባሲ ዜጎቹ ወደ ጎንደር እና ኦሮሚያ ክልል እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል።
ኢምባሲው በጎንደር ታጣቂ ኃይሎች በሚወስዱት የኃይል እርምጃ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ታች አርማጭሆ፣ ምእራብ አርማጭሆና ጭልጋ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት ባለመኖሩ ኖርዌያዊ ዜጎች ለስራም ሆነ ለጉብኝት ወደ ስፍራዎቹ እንዳይጓዙ አሳስቧል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባን አዲሱን ማስተር ፕላን በመቃወም በኦሮሚያ ክልል በተነሳው የተማሪዎችና የከተማ ነዋሪዎች ተቃውሞ ሳቢያ በክልሉ አስተማማኝ የሆነ መረጋጋት ስለሌለ ኖርዌያጂያን ዜጎች ወደነዚህ ስፍራዎች እንዳያቀኑ ኤንባሲው ማስጠንቀቂያውን በድረገጹ ላይ አስፍሯል።
ኢምባሲው በተለይ በአንቦ ዩንቨርሲቲና በሌሎች ዩንቨርሲቲዎች በሚገኙባቸው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የጸጥታው ሁኔታ አስጊ መሆኑንና ተቃውሞውን ተከትሎ እየተነሱ ያሉት ሕዝባዊ ቁጣዎች እየተጠናከሩ መቀጠላቸውን ገልጾ ፖሊስና የጸጥታ ኃይሎች የሚወስዱት የኃይል እርምጃዎች ችግሩን ማባባሱን አክሎ ገልጿል።
መንግስት በሰጠው መግለጫ ተቃውሞው እየተስፋፋ መምጣቱን አምኗል። አዲሱ መግለጫ መንግስት ሰሞኑን ተቃውሞውን በቁጥጥር ስር አውለነዋል፣ ተቃውሞው በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የሚካሄድ ነው በማለት ሲሰጥ ከበረው መግለጫ የተለዬ ነው።
ተቃውሞውን ኦነግና ግንቦት7 ን ጨምሮ በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፅንፈኛ አካላት የቀሰቁት ነው በማለት ገልጿል። ማስተር ፕላኑን ለመተው ፍላጎት የሌለው መሆኑንም ገልጿል።