በኦሮምያ የሚካሄደው ተቃውሞ ግለቱን ጨምሮ ቀጥሎአል

የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-እጅግ ደም አፋሳሽ እየሆነ በመጣው የኦሮምያ ተቃውሞ፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶች በአጋዚ ጥይት እየተረፈረፉ ነው። በምእራብ አርሲዋ ኮፈሌ ከተማ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎች ሲያልቁ፣ በርካቶችም ሆስፒታል ገብተዋል። በአሳሳ ትናንት የተገደለችው የ8 አመት ህጻን የቀብር ስነስርዓት ዛሬ የተፈጸመ ሲሆን፣ የከተማው ነዋሪ መንገድ በመዝጋት ተቃውሞን ገልጿል።

በምእራብ አርሲ ወደ ባሌ አቅጣጫ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኙ ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞው በከፍተኛ ሁኔታ በማየሉ፣ በርካታ የአጋዚ ሰራዊት አባላት ወደ አካባቢው ሲጓጓዙ ማርፈዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በምስራቅ ሀረርጌ ጉራዋ መንገድ ድሬ መንደር በሚባለው አካባቢም ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው። በአምቦ ደግሞ የከተማው እስር ቤት መቃጠሉን ለማወቅ ተችሎአል።

የዛሬው ተቃውሞው በአብዛኛው መንገዶችን በድንጋይ በመዝጋት የተከናወነ ሲሆን፣ በክልሉ ያለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መዳከሙም ተስምቷል። የአለማቀፍ ድርጅቶች ሳይቀሩ በመንገዶች መዘጋጋት የተነሳ በክልሉ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እያቆሙ ነው።

በምእራብ አርሲ የሟቹ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፎቶ ግራፎች ተቃጥለዋል። ማንኛውም የኦህዴድ ምልክት ያለበት አርማም እየተቃጠለ ነው። ኦህዴድ /ኢህአዴግ ከእንግዲህ አይገዛንም የሚሉ መፈክሮች በብዛት ይሰማሉ። መንግስት አሁንም ግጭቱን ከሃይማኖትና ዘር ጋር በማገናኝት ህዝቡን የሚከፋፍል ፕሮፓጋንዳ በመገናኛ ብዙሃን እየሰጠ እያስተላለፈ ነው።

ከሰዓት በሁዋላ በደረሰን ዜና ደግሞ በአሳሳና ዶዶላ ማንም ሰው ከቤት እንዳይወጣ በመታገዱ፣ ህዝቡ በረሃብ ልናልቅ ነው በማለት የድረሱልን ጩኸት በማሰማት ላይ ነው። ብዙ ወጣቶችም ከቤታቸው እየተያዙ በመታሰር ላይ ናቸው።