በኦሮምያ የመንግስት ሰራተኞች ለኦህዴድ በግዳጅ የሚከፍሉት ክፍያ እንዲቆም ጠየቁ

ሚያዝያ ፫ (ሦስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ አንዳንድ ወረዳዎች የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ለኦህዴድ ማጠናከሪያ በሚል ለአመታት ያለፈቃዳቸው ከደሞዛቸው የሚቆረጠው ገንዘብ እንዲቆም ጥያቄ አቅርበዋል።
በክልሉ ውስጥ የሚኖር የየትኛውም ብሄር ተወላጅ ከደሞዙ 5 በመቶ ለኦህዴድ በግዴታ ይከፍላል።
በጅማ ዞን በሚገኙት ሰቃ፣ ደዶ እና ጎማ ወረዳዎች የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች ከእንግዲህ ክፍያ አንከፍልም በማለት ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን፣ ከእንግዲህ ደሞዛችን በግድ የሚቆረጥ ከሆነ የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ሌሎችም በርካታ ወረዳዎች ክፍያው እንዲቋረጥ ማመልከቻ ማስገባታቸው ታውቋል።
በቅርቡ በአፋር ክልል በአዋሽ አርባ የሚገኙ መምህራንም እንዲሁ ለብሄር ብሄረሰቦች ዝግጅት በሚል የደሞዛቸውን 50 በመቶ እንዲሰጡ በተጠየቁበት ወቅት ተቃውሞአቸውን ገልጸው ነበር።