በኦሮምያ ክልል ልዩ የቁጥጥር ስርዓት ተዘረጋ

ታኀሳስ ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ በክልሉ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ፖሊስ አዲስ የቁጥጥር ስርዓት ዘርግቶ ህዝቡን በማስፈራራት ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ማንኛውም ሰው በክልሉ በሚገኙ ሆቴሎች አልጋ ለመያዝ እንዲሁም ለስራ ወይም ለሌሎች ጉዳዮች ሲንቀሳቀስ ከተገኘ ተይዞ ይጠየቃል:፡
በተለይ ሆቴሎች አዲስ ልዩ ቅጽ እንደሚሉ እየተገደዱ ሲሆን፣ በቅጹ ላይ አልጋ የሚይዘው ሰው በአካባቢው ለምን እንደተገኘ መናገር ይኖርበታል። የሆቴል ባለቤቶች እንደሚሉት እንዲህ አይነት ረጅም መጠየቅ የያዘ ቅጽ ሲቀበሉ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።
በሌላ በኩል ሰማያዊ ፓርቲ የታሰሩበትን አባሎች በማስመልከት መግለጫ አውጥቷል ፓርቲው ‹‹ሕዝባዊ መንግስት መመስረትና የሐገር ሉዓላዊነት መጠበቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው›› በሚልታህሳስ 20/2008 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ ፣ ኢትዮጵያ የምትገኝበት አስከፊ ሁኔታ ዘርዝሯል።
መንግስት 86 ዜጎችን በግፍ ከገደለ በሁዋላ በሌሎች ለማሳበብ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ድርጅት ንቁ አባላትንና ጋዜጠኞን ማሰሩን የገለጸው ሰማያዊ ፓርቲ፣የፓርቲው ልሳን የሆነውን የነገረ ኢትዮጵያን ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ሽፈራውን፣ የፓርቲውን ንቁ ታሳታፊ አባል ዮናታን ተስፋዬ፣ ቴዎድሮስ አስፋው፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርምያስ ጸጋዬና ፍሬው ተክሌና ሌሎችም ተደብድበው መታሰራቸውን ገልጿል። የኦፌኮ ም/ል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባና የፓርቲው ም/ል ጸሃፊ አቶ በቀለ ጣፋ መታሰራቸውን ያወሳው ፓርቲው፣ አገዛዙ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆችን ተራ በተራ እየለቀመ ወደ እስር ቤት እየወረወራቸው ነው ብሎአል።
በሃገራችን የደረሰውን ግፍና በደል የማስቆምና ህዝባዊ መንግስት የማቋቋም እንዲሁም የአገርን ክብር እና ሉአላዊነት ለማስከበር የጥቂቶች ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ህዝብ ድርሻ በመሆኑ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የቁርጠኛ ልጆቻቸውን ጥሪ በመቀበል ቆርጠው እንዲነሱ ጥሪ አቅርቧል።