በኦሮምያ እና ጉራጌ ዞኖች የመካሄደው የስራ ማቆም አድማ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርጓል

በኦሮምያ እና ጉራጌ ዞኖች የመካሄደው የስራ ማቆም አድማ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርጓል
(ኢሳት ዜና የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ/ም) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመቃወም በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን ጨምሮ በብዙ የኦሮምያ ክልል ከተሞችና በጉራጌ ዞን በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች እንዲሁም በስልጤ ዞን በሚገኙት በስልጤና ቡታጅራ የተጠናከረ የስራ ማቆም አድማ በመደረግ ላይ ነው።
አድማው በአሸዋ ሜዳ፣ አንፎ፣ ቀርሳ፣ ቡራዩ፣ ሰበታ፣ አለምገና ቢሾፍቱ፣ ወልቂጤ፣ መቱ፣ ሻሸመኔ፣ ጭሮ፣ ሞያሌ፣ ነቀምት፣ ወሊሶ፣ ሱሉልታ፣ ጅማ፣በአርሲ የተለያዩ ከተሞች : በባሌም በባሌ ሮቤ፣ አጋርፋ ፣ ጎባ ፣ ጊኒር፣ ደሎ ሰብሮ፣ መቱ፣ ሂርና እንዲሁም በ20 የምስራቅ ሃረርጌ ወረዳዎች የንግድ ድርጅቶች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል።
በሌሎችም ከተሞች የስራ ማቆም አድማው በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት መስሪያቤቶችና የንግድ ተቋማት ሙሉ ተዘግተዋል። ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ ክልሎች የሚሄዱ መስመሮች በመቋረጣቸው የአዲስ አበባ መናሃሪያ ዝግ ሆኖ ውሎአል።
በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ሲያወጡ ታይቷል።
ከፍቼ ወደ አዲስ አበባ፣ ከደገም ወደ አዲስ አበባ፣ ከጎሃጽዮን ወደ አዲስ አበባ ፣ ከሙካጡሪ ወደ አዲስ አበባ ይካሄድ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል። ሱሉልታ አካባቢም አንድ የአጋዚ ወታደሮችን የጫነ ኦራል መኪና በመገልበጡ 5 ወታደሮች ህይወታቸው ሲያልፍ 17 ወታደሮች ደግሞ መቁሰላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አንድ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ ከጅማ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ በወታደሮች ተገዶ ከወጣ በሁዋላ ከጅማ 90 ኪ/ሜ ርቀት በምትገኘው አሰንዳቦ ከተማ ላይ ሲደርስ ህዝቡ አስቁሞ የመኪናውን መስታውት መሰባበሩን ተከትሎ በአካባቢው የሚካሄድ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ሆኗል። ወታደሮች ግን ሾፈሮች በግድ ስራ እንዲጀምሩ ቢያስገድዱም፣ ሾፈሮች ግን አሻፈረን ብለዋል።
በከተማዋ ወደ 11 ሰዓት አካባቢ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር አንዳንድ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በሃረር ከተማ የመከላከያ አባላት የተዘጉ ሱቆችን ሲያሽጉ ውለዋል። የንግድ ቢሮ ሰራተኞች በፍርሃት ወደ ከተማ መውጣት ባለመቻላቸው የመከላከያ አባላት ራሳቸው እሸጋውን አከናውነዋል። በግዳጅ ከሃረር ከተማ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ የጀመሩ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች መንገድ ላይ በድንጋይ ተሰባብረዋል።
በጉራጌ ዞን በሁሉም ወረዳዎች ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።
ተከትሎ በህዝቡ ላይ ሽብር ለመፍጠር ወደ ከተማው ታንክ እንዲገባ ተደርጓል። የአካባቢው ነዋሪዎች ካለፉት 26 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ታንክ ማየታቸውን በአድናቆት ተናግረዋል። ከትናንት ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአጋዚ ወታደሮች ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
በጉብሪንና ወልቂጤ ላይ ወጣቶች እየተያዙ ታስረዋል። በዞኑ የሚኖሩና አዲስ አበባ የሚገኙ አንዳንድ የጉራጌ ባለሃብቶች አድማውን ታስተባብራላችሁ ተብለው መታሰራቸውን ገልጸዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ገብረጉራቻ ከተማ ላይ ደግሞ አካባቢውን ለመቆጣጠር ያስቸላል የተባለ 15 ሺ ጦር መስፈሩ ታውቋል። ህዝቡ ሰራዊቱን ውሃና ምግብ መከልከሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ማምሻውን ደግሞ በቡራዩ በርካታ ወጣቶች ታፍሰው መወሰዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጽደቁን ተከትሎ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በተነሳው ተቃውሞ በጊንጪና በአምቦ እስካሁን 6 ሰዎች በወታደሮች ተገድለዋል።