የካቲት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ላለፉት 4 ወራት በተከታታይ ሲደረግ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል።ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአጋዚ ሰራዊት በሰፈነበት ምእራብ ሃረርጌ፣ሀብሩ ወረዳ ዴፎ ከተማ ህዝቡ ለተቃውሞ በመውጣት፣ መሰረታዊ የሚባሉ የመብት ጥያቄዎችን ሲጠይቅ አርፍዷል።በወለጋ ሆድሮጉድሩ የሻምቡ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም እንዲሁ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።
በክልሉ የሚገኙ በርካታ ትምህርትቤቶች የተዘጉ ሲሆን፣መንግስት ትምህርት ቤቶችን መክፈት ለተጨማሪ ተቃውሞ ምክንያት ይሆናል በሚል ውሳኔው በአርሲ፣ወለጋና ምእራብና ምስራቅ ሃረርጌ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ለተወሰኑ ሳምንታት እንዲቆዩ ፍላጎት እንዳለው ታውቋል።
በርካታ የአገር ሽማግሌዎች፣ ህዝቡን እንዲመክሩ በየአካባቢው የተላኩ ቢሆንም፣ህዝቡ ሊቀበላቸው አልቻለም።ህዝቡ ለአገር ሽማግሌዎች፣መንግስት የታሰሩትን ልጆቻችንን እንዲለቅልን ንገሩት፣ ለገደላቸው ደግሞ ተገቢውን ካሳ ይክፈል የሚሉና የተለያዩ ጥያቄዎችን እያቀረቡ እንደሚገኙ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሞ ህዝብ ነጻ አውጭ ድርጅት ኦነግ፣ ከ300 በላይ የኦሮሞ ልጆችን ህይወት የቀጠፈው ህዝባዊ ተቃውሞ ለውጤት እንዲበቃ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲነሱ ጥሪ አቅርቧል። ኦነግ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጸመው እልቂት፣ ህወሃት ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን ጥልቅ የሆነ ጥላቻ ያሳያል ብሎአል።በህዝቡ ላይ የደረሰው እልቂት በአለማቀፍ ፍርድ ቤቶች እንዲመረመር ኢትዮጵያውያን እና የአለማቀፍ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርጉም ጠይቋል።