መጋቢት ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኮሚኒኬሽን ሚኒስትርና የመንግስት ጋዜጠኞች በክልሉ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ከፍተኛ የሆነ የንብረት መውደም አስከትሏል በማለት ሲዘግቡ ቢቆዩም፣ ጠ/ሚኒስትሩ ግን በባለሀብቶች ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ከ100 ሚሊየን ብር የማይበልጥና ጉዳቱም አነስተኛ በመሆኑ ባለሀብቶቹን እንዳላስደነገጠ ተናግረዋል።
አቶ ሀይለማርያም ከመንግስታዊው ዜና አገልግሎት ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለምልልስ በሀገሪቱ ቱርክ፣ ቻይናና ህንድ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንዳላቸው፣ ባለሀብቶቹ መሰል ግጭቶችን ስለሚያውቁት አዲስ እንደማይሆንባቸውና ችግሩ
ስራቸውን ሊያስቆም እንደማይችል ተናግረዋል። “ባለሀብቶቹ የሚያዩት የስርአቱን ጥንካሬ እንጂ እዚህም እዚያም የተፈጠረ ነገር አይደለም፤ ነገሩ ቢያሳስባቸው እንኩዋን የሚጨነቁበት ጉዳይ አድርገን አላየነውም” ብለዋል።
የደረሰውን ጉዳት ደምረን አይተናል የሚሉት አቶ ሃ/ማርያም፣ ” ከ100 ሚሊየን ብር አይበልጥም፣ ኢንሹራንስ ለሌላቸው እንከፍላለን” ሲሉ ጉዳቱን አሳንሰው ለማየት ሞክረዋል።
በተያያዘ ዜና ከትላንት በስቲያ የኦሮሚያ አባገዳዎች በግጭቱ ለሞቱ ሰዎች የደም ካሳ እንዲሰጥ፣ የታሰሩ እንዲፈቱ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ጠ/ሚኒስትሩም መንግስት ካሳ ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እንደገና ወደ ስልጣናቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።ዶ/ር በላይነህ ” ስልጣን ፈላጊ ናቸው፣ ግጭት ይቀሰቅሳሉ” በሚል ተገምግመው ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ኦህዴድ ውሳኔ ካሳለፈ በሁዋላ፣ የዩኒቨርስቲው የቦርድ አባላት የሆኑት የምስራቅ እዝ የመከላከያ ሃላፊ ባደረጉት ግፊት እንደገና ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። ዶ/ር በላይነህ ከመከላከያ ባለስልጣናት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል።