የካቲት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የክልሉ የፍትህ ቢሮ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች በጻፈው ደብዳቤ ማንኛውም ባለጉዳይ አቤቱታዎችን በኮምፒዩተር ካላስጻፈ ጉዳዩ እንዳይታይለት ወስኗል። በክልሉ የሚገኙ ዳኞች በበኩላቸው ውሳኔው የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ እና የእድገት ደረጃ ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ይላል።
ዳኞች እንደሚሉት አብዛኛው ህዝብ አቤቱታዎችን አስጽፎ የሚያቀርበው በወረቀትና በእስክር ቢቶ ሆኖ ሳለ፣ የድሆችን የኑሮ ሁኔታ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ፣ በኮምፒዩተር ያልተጻፈ አቤቱታ ተቀባይነት እንዳይኖረው ብሎ መወሰን ፍትሀዊ አይደለም ።
አንድ ገጽ ለማስጻፍ እስከ 6 ብር እንደሚያስከፍል የሚገልጹት ዳኞች፣ 10 ገጽ አቤቱታ የሚየስጽፍ ባለጉዳይ እስከ 60 ብር መክፈል ግድ ይለዋል። በርካታ ድሆች አቤቱታ ለማቅረብ በሚሄዱበት ጊዜ፣ በኮምፒዩተር ካለስጻፋቸው ጉዳያችሁን አናይም እየተባሉ እንደሚመለሱ ዳኖች ለኢሳት ገልጸዋል።
አንዳንድ ዳኞች ውሳኔውን በመቃወም ለድሆች ለመሟገት ሙከራ ቢያደርጉም የመንግስትን ፖሊሲ ተቃውማችሁዋል በሚል ቅጣት እየደረሰባቸው ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች በከተማዎች ውስጥ አንድ ኮምፒዩተር ብቻ ያለ ሲሆን፣ ባለ ኮምፒዩተሮችም የፈለጉትን ዋጋ ያስከፍላሉ።