ኀዳር ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአዲስ አበባን አዲሱን ማስተር ፕላን በመተቸት በተማሪዎች የተጀመረው ተቃውሞ እያደገ፣ ህዝቡን በማሳተፍ በተለያዩ አካባቢዎች የቀጠለ ሲሆን ፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት በሚወስዱት እርምጃ የታዳጊወጣቶች ህይወት ተቀጥፏል።
በቦረና ዞን ዱጋዳዋ ወረዳ ፍንጭ ውሃ ከተማ ላይ ተነስቶ በነበረው ተቃውሞ ተማሪ ቢፍቶ ኮንሶ የተባለች የ10ኛ ክፍል ተማሪ ፖሊሶች የተኮሱት አስለቃሽ ጭስ አፍኗት ስትወድቅ ፣ የ7 ወሯ ነፍሰ ጡር እህቷ ወ/ሮ መድሃኒት ኮንሶ እህቷን ለመታደግ በላዩዋ ላይ ስትወድቅ ጭሱ እሷንም አፍኗት ወደ ፍንጭ ውሃ ጤና ጣቢያ ከተወሰደች በሁዋላ፣ እንዳስወረዳት ታውቋል።
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ የተነሳው ተቃውሞ ወደ ገጠር ከተማዎችም መስፋፋቱ ታውቋል። በኢበላ ቀበሌ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ከኢቦ ዲዲሳ ቀበሌ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር በጋራ በመሆን ወደ ቁርቁባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አምርተው በጋራ ተቃውዋቸውን ሲያሰሙ ውለዋል። ተማሪዎቹ ” ዲሞክራሲያዊ መብት ይከበር፣ መንግስት መሬት በመሸጥ አገር አልባ እያደረገን ነው።” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።የጸጥታ ሃይሎች ሰልፉን በሃይል ለመበተን ቢሞክሩም የመማር ማስተማሩ ሂደት ግን ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል። በዚሁ ወረዳ በሱሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ተመሳሳይ ተቃውሞ ተደርጓል።
የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች ተቃውሟቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ከሰራተኞች መካከል አንዱ የሆኑት የ4 ልጆች አባት አቶ ኤቢሳ ቱጆ በፖሊሶች መገደላቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል። 5 ሰዎችም ክፉኛ ቆስለው ወደ አዲስ አበባ ለህክምና ተልከዋል።
በምራብ ሸዋ ጌዲዮ ከተማ የመንግስት ሰራተኞች ከካቢኔ አባላት ጋር በመቀላቀል ሲቃወሙ ውለዋል። በጀልዱ ከተማም እንዲሁ የመንግስት ሰራተኞችን ያሳተፈ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።በጊንጭ የነበረው የስፖርት ፌስቲቫል በተቃውሞ ሲሰረዝ፣ በኮልኮ ቢኒ ከተማ በህዝብ እና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ አለመግባባባት አንድ ፖሊስ መገደሉን መረጃዎች ጠቁመዋል። በአርሲ ዞን ኮኮታ ወረዳም እና በወሊሶ ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። በወሊሶ ተቃውሞው እየጠነከረ መሄዱን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው አውራ ጎዳና በድንጋይ ተዘግቷል። በአዳማ ዩኒቨርስቲም ተማሪዎች በፖሊሶች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ አርፍደዋል።ፖሊሶችም በአጸፋው ተማሪዎችን ደብድበዋል። የዩኒቨርስቲው ተማሪዎችረ አብዛኞቹ ግቢውን ለቀው ወጥተዋል።
በየአካባቢው ከሚደርሱን መረጃዎች ለመረዳት እንደሚችላው፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተነሳው ተቃውሞ ከ7 ያላነሱ ተማሪዎች ተገድለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩም መጠነኛና ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።