ሚያዝያ ፲ (አሥር) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች ተነስቶ የነበረውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ የገዢው ፓርቲ ወታደሮች ያደረሱትን ጭፍጨፋ በገለልተኛ ወገኖች ለማጣራት ያቀረቡትን ጥያቄ ኢህአዴግ ውድቅ አድርጎታል።
ቢቢሲ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ጠቅሶ እንደዘገበው በአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችም ሆነ በመንግስታት የቀረበውን ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ የማቋቋም ሃሳብ በአገዛዙ በኩል ተቀባይነት አላገኘም። አቶ ሃይለማርያም ኢትዮጵያ ምርመራውን በራሷ የማካሄድ ብቃት አላት ሲሉ ለክልከላው ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።
በቀድሞው ምክትል የምርጫ ቦርድ ሃላፊ በነበሩት የህወሃት አባሉ በዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚዓብሄር የሚመራው የሰብአዊ መብት ኮሚሺን ብቻ ምርመራ ማካሄድ እንደሚችል በመግለጽ አቶ ሃይለማርያም የኢህአዴግን አቋም ግልጽ አድርገዋል።
በገዢው ፓርቲ የተመሰረተው ተቋም ገለልተኛ እንዳልሆነ በራሱ በኢህአዴግ ባለስልጣናት ሳይቀር የሚታመንበት ቢሆንም፣ አቶ ሃይለማርያም ግን ተቋሙ የብቃት እንጅ የገለልተኝነት ችግር የለበትም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዋነኝነት በሁለቱ ክልሎች የተካሄዱ ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎች በስራ አጥነት ምክንያት የመጡ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሃይለማርያም፣ በሁለቱ ክልሎች ብቻ እንዴት ስራ አጥነት ለእንቅስቃሴው መነሻ ሊሆን እንደቻለ ግን ማብራሪያ አልሰጡም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዶ/ር አዲሱ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በሶስት ክልሎች ምርመራ አድርጌ በህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴው ወቅት በኦሮምያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች ፖሊሶችንና ወታደሮችን ሳይጨምር 606 ሰዎች መገደላቸው ገልጿል። የኢሳት ወኪል እንደገለጸው ገዢው ፓርቲ አይቶ እንዲተላለፍ የወሰነው ሪፖርት 606 ሰዎች መገደላቸውን ከገለጸ፣ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ሊሆን እንደሚችል የድርጅቱን የፕሮፓጋንዳ አሰራር በማየት አስተያየቱን ሰጥቷል።
ኮሚሽኑ 462 ሰላማዊ ሰዎች እና 33 ወታደሮች በኦሮምያ መገደላቸውን ጠቅሶ፣ በኦሮምያ ለተነሳው አመጽ አንዳንድ የታች አመራሮችን፣ ኦነግን፣ ኦፌኮንና ኦኤም ኤን ሚዲያን ተጠያቂ አድርጓል። በአማራ ክልል ተገደሉ ላላቸው 110 ሰዎች የእንቅስቃሴው መነሻ ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ ኢሳትን በመሳሰሉ የሽብር መጠቀሚያ ሚዲያዎች መልዕክቶች ተላልፏል ሲል የሚዲያ ተቋሙን ተጠያቂ አድርጓል።
ኮሚሽኑ የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከሃላፊነት ነጻ በማድረግ፣ አንዳንድ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ የክልል አመራሮችን እና ወታደሮችን ተጠያቄ በማድረግ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ የሚቀርበውን ጫና ለመቀነስ ሙከራ አድርጓል።
ይሁን እንጅ የቀረበው የሟቾች ቁጥር ይበልጥ ምርመራ እንዲካሄድ የሚያደርግ እንጅ “ በቃ ተብሎ የሚተው አይደለም “ ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።
በሌላ በኩል አሁንም ዜጎችን እያሳደዱ ማሰር መቀጠሉ ታውቋል። በተለይ በሰሜን ጎንደር በተለያዩ ወረዳዎች ዜጎች በየጊዜው ከቤታቸው እየተወሰዱ ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን፣ አንዳንዶች ወዲያውኑ ሲለቀቁ ሌሎች ደግሞ ለተጨማሪ ምርምራ በሚል ወደ እስር ቤት ይወሰዳሉ።
በተለይ ከቀድሞዎቹ የአንድነት እና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ ሰዎች እየተመረጡ እየተያዙ መሆኑን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።