ጥር ፲ ( አሥር )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የሚመራው የሶማሊያ ልዩ ሃይል ወደ ቦረናና ጉጂ ዞኖች በማምራት በህዝቡ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ የአካባቢው ታጣቂዎች በወሰዱት እራስን የመከላከል እርምጃ በርካታ የሚሊሺያ አባላት ሲገደሉ 4 መትረየሶችን ጨምሮ በርካታ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች ተማርከዋል።
ጉጂና ቦረናዎች የወሰዱትን እርምጃ ተከትሎ በምስራቅ ሃረርጌ የጉርሱም፣ ሚደጋ ቶላ እና ጪናቅሶ ወረዳዎች ነዋሪዎች እንቅስቃሴ የጀመሩ ሲሆን አካባቢውም በውጥረት ተሞልቷል። ነዋሪዎች “ከዚህ በሁዋላ መንግስትን አንጠብቅም የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን” ያሉ ሲሆን፣ ውጥረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ባለፉት 2 ሳምንታት የሶማሊ ክልል ልዩ ሚሊሺያዎች ባደረሱት ጥቃት በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች መገደላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ችግሩን በማስመልከት የኦሮምያና የሶማሊ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት አዳማ ላይ ተሰብስበው የነበረ ሲሆን፣ የአንዱ ክልል ባለስልጣን ሌላውን መውቀሱን ምንጮች ገልጸዋል። የሁለቱን ክልሎች ድንበር በፍጥነት ለማካለልም ተወስኗል።
ይሁን እንጅ ህወሃት በኦሮምያ ተነስቶ የነበረውን የህዝብ ንቅናቄ ለመበቀል የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲን ተጠቅሟል የሚል ቅሬታ በአንዳንድ የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ዘንድ መኖሩን ምንጮች ገልጸዋል።