ኢሳት (ጥር 13 ፥ 2008)
ከቀናት በፊት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዳግም ያገረሸው ተቃውሞ አርብ መቀጠሉን ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
በምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በምስራቁ ሃረርጌ አካባቢዎች በትንሹ ስድስት ሰዎች መገደል ምክንያት የሆነው ተቃውሞ ቀጥሎ የሚገኝ ሲሆን በርካታ ነዋሪዎችም ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል።
ከሁለት ሳምንት በላይ ትምህርትን ያቋረጡ ዩኒቨርስቲዎችም ትምህርታቸውን ያልጀመሩ ሲሆን የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት ተማሪዎችና ነዋሪዎች ምክክርን እያካሄዱ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።
ይኸው አለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ የሚገኘው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ሲል አንድ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም ከቀናት በፊት ማሳሰቡን መዘገባችን ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተቃውሞ በቁጥጥር ስልር ዉሏል ቢሉም የአውሮፓ ህብረት የአሜሪካና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ቀጥሎ የሚገኘውን ተቃውሞና መንግስት እየወሰደ ያለውን የሃይል እርምጃ አሳስቧቸው እንደሚገኝ በመግለጽ ላይ ናቸው።