ኢሳት (ጥር 2 ፥ 2008)
በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሰኞ በምስራቅና በምዕራብ ሃረርጌ አካባቢዎች መቀጠሉ ተገለጠ።
በመለስተኛ ከተሞች በተካሄደው በዚሁ ተቃውሞ፣ ነዋሪዎችና ተማሪዎች ለእስር የተዳረጉ ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥያቄ ማቅረባቸው ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በምዕራብ ሃረርጌ ጭሮ ከተማና አካባቢዋ ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አለመርገቡንና ተመሳሳይ ተቃውሞዎች በምስራቅ ሃረርጌ በሚገኙ ከተሞች ሲካሄድ ማርፈዱም ታውቋል።
በምዕራብ ሃረርጌ ሜዔሶ ወረዳና አካባቢው በተካሄደው በዚሁ ተቃውሞ በርካታ ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት ግድያና እስራት እንዲቆም መጠየቃቸው ከተለያዩ ምንጮች ለመረዳት ተችሏል።
በሳምንቱ መገባደጃ ሂርና ከተማን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች በተካሄዱ ተቃውሞዎች የጸጥታ ሃይሎች እርምጃን በመውሰድ በትንሹ ሁለት ሰዎች መገደላቸው መዘገቡ ይታወሳል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው ዳግም አገርሽቶ ያለው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ለበርካታ ሰዎች መገደልና እስራት ምክንያት መሆኑን በድጋሚ ገልጸዋል።
የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ባለው እርምጃም እስካሁን ድረስ በትንሹ 140 ሰዎች መገደላቸውንና የሟቾቹ ቁጥር በየእለቱ እየጨመረ መሆኑን አስታውቀዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞው በቁጥጥር ስር ውሏል ቢሉም ትምህርት በተቋረጡባቸው ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲቀጥል ለማድረግ ድርድር እያካሄዱ እንደሆነም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።