በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል

ኢሳት (ሃምሌ 20 ፥ 2008)

ከቀናት በፊት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ዳግም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ረቡዕ መቀጠሉ ታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ማክሰኞ ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የሃይል እርምጃን እንደሚወስድ  ማሳሰቢያን ቢሰጥም በተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ተቃውሞ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በዞኑ እየተካሄደ ባለው በዚሁ ተቃውሞ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና አምስት ሰዎች ዳግም ጉዳት እንደደረሰባቸው የኦሮሚያ ኪልል መንግስት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

ይሁንና፣ በአካባቢው ያለው ተቃውሞ እልባት ባለማግኘቱና የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱት እርምጃ በመጠናከሩ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል።

የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ተቃውሞው ጸረ-ሰላም በሆኑ ሃይሎች የተቀነባበረ ነው ቢልም ተቃውሞን እያቀረቡ ያሉ ነዋሪዎች በክልሉ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዲፈቱ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።

በምዕራብ አርሲ ዞን እየተካሄደ ካለው ተቃውሞ በተጨማሪ በምስራቅ ሃረርጌና በምስራቅ ሸዋ ስር በሚገኙ ከተሞች ተመሳሳይ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በኦሮሚያ ክልል ዳግም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሰዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ የክልሉ መንግስት ከተቃውሞ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ አካላት በቁጥጥር ስር ለማዋል እርምጃን እየወሰደ እንደሆነ አስታውቋል።

ይሁንና በዘመቻው ምን ያህል ሰዎች ለእስር እንደተዳረጉና በአጠቃላይ በነዋሪዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።