ኢሳት (የካቲት 17, 2008)
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ዳግም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሃሙስ በበርካታ አካባቢዎች መዛመቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞን ለመቆጣጠር የሃይል እርምጃን እንደሚወስዱ ቢያሳስቡም ህዝባዊ ተቃውሞው በምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በምዕራብና ምስራቅ ሃረርጌ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል።
በየአካባቢው የሚኖሩ ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለውን ግድያና የጅምላ እስራት በመቃወም ድርጊቱን ሲያወግዙ መዋላቸው ተገልጿል።
ይሁንና፣ የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞውን ለመበተን በወሰዱት እርምጃ ቁጥራቸው በትክልል ሊታወቅ ያልተቻለ ነዋሪዎች መገደላቸውንና ጉዳት የደረሰባቸውም በየህክምና መስጫ ጣቢያዎች መታየታቸውን የተለያዩ አካላት አስታውቀዋል።
በክልሉ በየዕለቱ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር በመጨመር ላይ በመሆኑም የሟቾችን ቁጥር በአንድ ጊዜ መግለፁ አዳጋች እንደሆነ የፓርቲና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች በመግለጽ ላይ ናቸው።