ጥር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የኢሳት የኦህዴድ ምንጮች እንደገለጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ከ3 አመት በፊት የተመረጡት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ከተመረጡበት ማግስት ጀምሮ በህመም ምክንያት በስራቸው ላይ ለመገኘት ባይችሉም እርሳቸውን ለመተካት በኦህዴድ ባለስልጣናት መካከል ስምምነት በምጥፋቱ ተተኪ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ አልተቻለም።
አቶ አለማየሁ አቶምሳ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በሁዋላ አንዳንድ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚናገሩት በምግብ መመረዝ ሳቢያ በተነሳ ችግር እስካሁን ድረስ ስራቸውን በተገቢው ሁኔታ ለመፈጸም አልቻሉም።
በአቶ መለስ ዜናዊ የቀብር ስነስርአት ላይ ህክምናቸውን ሳይጨርሱ እንዲገኙ ተጠርተው የነበሩት አቶ አለማየሁ፣ የቀብር ስነስርአቱ ከተፈጸመ በሁዋላ ብዙም ሳይቆዩ አቋርጠውት የነበረውን ህክምና ለመከታተል ወደ ታይላንድ አቅንተዋል። ዜናውን እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ አቶ አለማየሁ በታይላንድ ህክምናቸውን እያደረጉ ሲሆን፣ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ካለፈው ምክር ቤት ስብሰባ ጀምሮ እሳቸውን ለመተካት በተደጋጋሚ ቢሰበሰቡም ስምምነት ላይ ለመድረስ ባለመቻላቸው ምክትላቸው እሳቸውን ተክተው በመስራት ላይ ናቸው።
በክልሉ ምክር ቤት ህገደንብ አንድ ፕሬዚዳንት በህመም ወይም በሌላ ምክንያት በቦታው ላይ ለአመታት ካልተገኘ ስለሚወሰድበት እርምጃ የተደነገገ ነገር አለመኖሩን የኦህዴድ አባሉ ምንጫችን ገልጿል። በዚህም የተነሳ አቶ አለማየሁ በጽህፈት ቤታቸው ሳይገኙ ቀጣዩ ምርጫ ከሁለት አመት በሁዋላ ይከናወናል በማለት ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ በሙሉ ጤንነት ወደ ስልጣናቸው ይመለሳሉ ብለው እንደማያምኑ ምንጫችን ገልጸዋል።
በአቶ አባዱላ ገመዳ የሚመራው ቡድን የአቶ አለማየሁን በስልጣን መቆየት የማይደግፍ ሲሆን፣ አቶ አባዱላ ተመልሰው የክልሉ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ለማድረግ ደጋፊዎችን እያሰባሰቡ ነው። በአቶ አለማየሁ ዙሪያ የተሰባሰቡ ሰዎች በበኩላቸው የአቶ አባዱላን ቡድን በሙስና በመክሰስ ተመልሰው ወደ ስልጣን እንዳይመጡ አስፋላጊውን ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በክልሉ ውስጥ ለሚታየው ሙስና ከፍተኛውን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አባሉ ገልጸዋል። “ሙስና ወረርሽኝ ሆኗል” ያሉት አባሉ ” በሙስና ኔት ውርክ ውስጥ ያልገቡ አባሎች እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ከስራ እየተባረሩ መሆኑን” ገልጸዋል። የአፈ ጉባኤ የአባዱላ ደጋፊዎች በአንድ በኩል ስልጣናችንን ብናጣ በሚል በዘረፋ ውስጥ ሲሰማሩ፣ የአቶ አለማየሁ ቡድኖችም እንዲሁ የአባዱላ ቡድን አሸንፎ ስልጣን ቢይዝ ከስራ ይቀንሰናል በሚል ከፍተኛ ዘረፋ እየፈጸሙ መሆኑን ገልጿል።
በክልሉ ስለሚፈጸመው ሙስና የጸረ ሙስና ኮሚሽንን ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።