ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2008)
የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ ዙሪያ ሊተገበር የተዘጋጀውን ማስተር ፕላን በመቃወም ሰላማዊ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎችን መግደሉን፣ መደብደቡንና፣ ማዋከቡን አጠናክሮ መቀጠሉ ታወቀ።
በኦሮሚያ ስላለው ስለወቅታዊ ሁኔታ አጠቃላይ ሁኔታ ዝርዝር እንዲሰጡን የተጠየቁት ዶ/ር መረራ፣ በመንግስት ሃይሎች ዜጎችን የማሰሩ ሄደት አሁንም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ተናግረዋል። ባለፈው እሁድ በሃገረማሪያም ይኖር የነበረ አንድ የኦፌኮ አመራርና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመንግስት ሃይሎች ተይዘው እንደታሰሩ ዶ/ር መረራ ለኢሳት ገልጸዋል።
የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የተቃውሞው አስተባባሪዎች ናቸው ያላቸውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራር አባላት አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ቱፋ እና የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊ የነበሩት አቶ ጉርሜሳ አየነውን ማሰሩን መዘገባችን ይታወሳል። በቅርቡም የአቶ በቀለ ነጋአ በቁም እስር እንዲሆኑ እንደተደረገ ታውቋል። አቶ በቀለ ነጋአ በቁም እስር ላይ እያሉ ለሚዲያ ምንም አይነት መረጃ እንዳይሰጡና ወደ ቢሮ ወይም ወደ ፈለጉበት አካባቢ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ እገዳ እንደተጣለባቸው ለማወቅ ተችሏል።
እስካሁን ድረስ ከ4ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በማስተር ፕላን ሰበብ እንደታሰሩ ሲታወቅ፣ አሁንም በመላው ኦሮሚያ ተቃዋሚ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩትን ሁሉ እየታደኑ መታሰራቸው ተገልጿል። የታሰሩት የአመራር አባላትም አብዛኞቹ እስካሁን ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ በጸጥታ ሃይሎች ተከልክለዋል።
የኦሮሞ ኮንግሬስ አባላት ከመታሰራቸው ውጪ ምንም አይነት መረጃ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች አካላት ማግኘት እንዳልቻሉ ዶ/ር መረራ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
ዶ/ር መረራ “የኢትዮጵያ መንግስት የፖሊስ ወይም የህግ አካላት ያልሆኑ ከህግ ውጭ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች አሰማርቶ ባለበት ሁኔታ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ አቶ በቀለ ነጋአን ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት ሲል መጫን አይፈልግም” ብለዋል።
የደህንነት አካላት በአቶ በቀለ ነጋአ ቤተሰብ ላይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ማስፈራርያ እንደሰጧቸው መዘገባችን ይታወሳል። አቶ በቀለ ነገአ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ ወስነው መንቀሳቀስ ከፈለጉ መብታቸው እንደሆነም የደህንነት ሰዎች እንደነገሯቸው ለመገናኛ ብዙሃን ባሰራጩት ጹሁፍ አስታውቀው ነበር።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አባላት ቢታሰሩም ፓርቲው ስራውን አጠናክሮ መስራቱን እንደቀጠለ ለኢሳት የገለጹት ዶር መረራ፣ “መንግስት የተወሰኑ አባሎቻችንን ቢያስርብንም፣ አሁን በዋናነት መልሶ የማደራጀት ስራ እየሰራን ነው” ብለዋል።
በአዲስ አበባ እስካሁን ድረስ ለምን ሰላማዊ ሰልፍ እንዳላደረጉ ለተጠየቁት ጥያቄ ዶር መረራ ሲመለሱ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ሲፈልግ ህግን፣ ካልፈለገ የራሱን ህግ የሚጠቀም በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፍ ከልክሎናል ብለዋል። በመሆኑም ኢህአዴግ “አታደርጉም የሚል ውሳኔ ሲሰጥ ህገመንግስትን እየጣሰ፣ እኛ ግን ህግ ያልሆነውን የራሱን ህግ እንድናከብር የሚፈልግ ፓርቲ ነው” ብለዋል።
ሆኖም ዶ/ር መረራ ኢህአዴግ ፈቀደ አልፈቀደ ህዝቡ በየክፍለሃገሩ ለሰላማዊ ሰልፍ እየወጣ እንደሆነ አብራርተዋል። ትግሉ አዲስ አበባ ሲደርስ ሰላማዊ ህዝቡ ሰልፍ መውጣቱ አይቀሬ መሆኑን ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ዶር መረራ የኢትዮጵያ መንግስት የገባበት መንገድና ግትር አቋሙ እጅግ አደገኛ፣ ማንንም እንደማይጠቅም መሆኑን አስረድተው ወደ እርቅና ሰላም የሚያመጣ መንገድ መከተል እንደሚያስፈልግ መክረዋል። በመቀጠልም የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱ በጋራ እንዲታገል ዶ/ር መረራ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ተሰባስበው ህዝቡን በመምራት ለሁላችን የምትሆን ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚያስችል አቅጣጫ መቀየስ እንዳለባቸው ጥሪ አስተላልፈዋል።
በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተባብሶ መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ። በትናንትናው ዕለት በአዳማ ላይ አንድ ሰው ተገሎ መገኘቱንና፣ ሰሜን ሸዋ አቦቴ አካባቢ ሌላ ሰው ተሰቅሎ እንደተገኘ ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች ያለመክታሉ። በማስተር ፕላን ሰበብ የተነሳው ተቃውሞ በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደገና አገርሽቷል። በምዕራብ ሸዋ በሃረር መስመር ጨለንቆ እና ቆቦ ላይ በትናንትናው ዕለት የታሰሩት ይፈቱ የሚል ተቃውሞ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።