ኢሳት (ታህሳስ 27 ፣ 2007)
በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ከተሞች ዳግም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የጸጥታ ሃይሎች የቤት ለቤት ፍተሻንና የጅምላ እስርን በማካሄድ ላይ መሆናቸውን የተለያዩ አካላት ገልጸዋል።
የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ተቃውሞን ሲያስተባብሩ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች የዚሁ ሰለባ መሆናቸውንም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ሂውማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግድያ ከተፈጸመባቸው ሰዎች በተጨማሪ በርካታ ተማሪዎችና ነዋሪዎች ለእስር እየተዳረጉ እንደሆነ አስታውቋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ በበኩሉ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ባለው በዚሁ ዘመቻ ከ4ሺ የሚበልጡ አባላትና ደጋፊዎች መታሰራቸውን ገልጿል።
የጸጥታ ሃይሎች መሳሪያን የታጠቁና የደበቁ ሰዎች አሉ በማለት በምዕራብ የኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች የቤት ለቤት ፍተሻን እያካሄዱ እንደሚገኝ ታውቋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ለእስር ስለተዳረጉ ሰዎች ቁጥር መረጃን ባይሰጡም ሁከትና ብጥብት አስነስተዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።
በጸጥታ ሃይሎች የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑንም የሟቾችን ቁጥር በትክክል ማወቅ እንዳልተቻለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ገልጸዋል።
የፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው በመንግስት እርምጃ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ125 በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።