ኢሳት (ታህሳስ 27 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ወደ 70ሺ አካባቢ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን አሶሼትድ ፕሬስ የፓርቲ አባላትን ዋቢ ባማድረግ ዘገበ።
የክልሉ መንግስት በበኩሉ በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው በቅጣት ላይ የነበሩ 10ሺ እስረኞች በይቅርታ እንዲፈቱ መደረጉን ሃሙስ ይፋ አድርጓል።
ይሁንና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ 70 ሺ አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች በኦሮሚያ ክልል ብቻ ለእስር መዳረጋቸውን በዜና አውታሩ አስታውቀዋል።
የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በአስቸኳይ አዋጁ ምክንያት የጅምላ እስራት ሲካሄድ መቆየቱን የሃገር ውስጥና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ይገልጻሉ።
መንግስት በዘመቻው ከ21 ሺ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ቢያረጋግጡም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች ቁጥሩ በእጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል ለመገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ ቆይተዋል።
አብዛኞቹ እስር ቤቶች በአሁኑ ወቅት ሞልተው እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ሙላቱ ገመቹ የግል መኖሪያ ቤቶች ሳይቀር ለእስር ቤት እያገለገሉ እንደሚገኝ ለአሶሼትድ ፕሬስ አስረድተዋል።
ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከ600 የሚበልጡ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ይገልጻል።
የመንግስት ባለስልጣናት በዚሁ የጸጥታ ሃይሎች ዕርምጃ ወደ 500 አካባቢ ሰዎች መሞታቸውን ማረጋገጣቸውን ይታወሳል። ይሁንና የተባበሩት መንግስታትን ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ግድያውን በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት ጥያቄን ቢያቀርቡም መንግስት ተባባሪ እንደማይሆን ምላሽን ሰጥቷል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ረቡዕ በምህረት እንዲለቀቁ የተደረጉት 10ሺ እስረኞች በእስር ቆይታቸው መልካም ስነምግባር ያሳዩና ከጥፋታቸው የታረሙ መሆናቸው በመረጋገጡ ነው ሲል አስታውቋል።
እስረኞቹ የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው ከ13 አመት በላይ በእስር ላይ የቆዩ እንዲሁም ከስድስት ወር እስከ 25 አመት የእስር ጊዜያቸውን የጨረሱ መሆናቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።