መስከረም 26 ፥ 2009)
በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ዳግም የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ሃሙስ ለአምስተኛ ቀን ቀጥሎ በአርሲ ዞን ስር በምትገኘው የአጄ ከተማ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎችን ጨምሮ ነዋሪዎች መገደላቸውን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ።
በሳምንቱ መገባደጃ እሁድ በቢሾፍቱ ከተማ ከእሬቻ አከባበር ወቅት ጋር በተገናኘ የደረሰውን ዕልቂት ተከትሎ በምዕራብና ምስራቅ አርሲ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ መቀስቀሱን መዘገባችን ይታወሳል።
ይኸው ተቃውሞ ዕልባትን አለማግኘቱን ለኢሳት የተናገሩት ነዋሪዎች ሃሙስ በአጄ ከተማና አካባቢው ለሰዓታት የቆየ የተኩስ ልውውጥ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎችና በታጠቁ ነዋሪዎች መካከል ሲካሄድ መዋሉን ገልጸዋል።
ህዝባዊ ተቃውሞን ለመቆጣጠር በተወሰደ የሃይል ዕርምጃና በተፈጠረው ግጭት ከ10 የሚደርሱ ነዋሪዎች መገደላቸውን እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
ይሁንና በአካባቢው ደርሷል ስለተባለው የሞት አደጋ የክልሉ መንግስትም ሆነ ሌሎች አካላት የሰጡት ማረጋገጫ የለም።
በአርሲ ነገሌ ላንጋኖ እንዲሁም በሌሎች አጎራባች የምዕራብ አርሲ ዞን አካባቢዎች ተመሳሳይ ህዝባዊ ተቃውሞ በመካሄድ ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሰኞ በሰጠው መግለጫ፣ በአካባቢው በተቀሰቀሰው አዲስ ግጭት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለፁ ይታወሳል።
ሃሙስ በአካባቢው የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ግን የክልሉ መንግስት እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የሌለ ሲሆን ተመሳሳይ ተቃውሞዎች በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ባሉ የክልሉ ከተሞች ከቀናት በፊት መካሄዱ የሚታወቅ ነው።
ለአንዲት አሜሪካዊት ሞት ምክንያት የሆነው ይኸው ተቃውሞ በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ ዳርቻ ባሉ የመኖሪያ የንግድ ተቋማት ዙሪያ ስጋት አሳድሮ መቀጠሉን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በምስራቅና ምዕራብ አርሲ ዞን አካባቢ በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎሉንም ለመረዳት ተችሏል።