ኢሳት (የካቲት 23 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል ዳግም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሁለት ከፍተኛ አመራሮችን ከሃላፊነት አነሳ።
በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን የስልጣን ክፍተት ለመሙላትና ዳግም ባገረሸው ተቃውሞ ዙሪያ ለመምከርም ኦህዴድ በአዳማ ከተማ ከረቡዕ ጀምሮ የሚካሄድ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱንም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የኦህዴድ ጽ/ቤት ሃላፊና የኢህአዴግ ስራ አስፋጻሚ የነበሩት አቶ ዳባ ደበሌና የፓርቲው የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና የጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ሰለሞን ኩሉ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉ አመራሮች መሆናቸው ታውቋል።
ፓርቲው በቅርቡ ባካሄደው ግምገማ አመራሮቹ የነደፏቸው መዋቅሮች ችግሩን ለመቅረፍ ያበረከቱት አስተዋጽዖ አነስተኛ ነው በሚል ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መወሰኑ ተገልጿል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ ገቢዎች ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ የኦህዴድ ጽ/ቤት ሃላፊ ተደርገው የተሾሙ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ የጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ በዙ ዋቅቤካ ደሞ የኦሮሚያ የአስተዳደርና የፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ሆነው መሾማቸውም ታውቋል።
ፓርቲው በአዳማ ከተማ እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ስብሰባም ሌሎች አመራሮች ላይ ተመሳሳይ እርምጃን ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የመንግስት ባለስልጣን ተቃውሞን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን በመሄድ ላይ ቢሆኑም ተቃውሞው በተያዘ ሳምንት በምዕራብ ሸዋ እና እንዲሁም በምስራቅ ሃረርጌ አካባቢዎች ቀጥሎ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።