ጳጉሜ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ጳጉሜ አንድ ቀን የጀመረው የኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ እንቢተኝነት አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በአዳ በርጋ፣ ጊኒር ፣ ሙገር፣ ዶዶላ፣ አምቦ፣ ነቀምቴ፣ ጉደር፣ ደደር፣ ቡራዩ፣ ሱሉልታ እንዲሁም በምስራቅ ሃረርጌ የንግድ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል። የፀጥታ አስከባሪዎች በግዳጅ የንግድ ድርጅቶችን ለማስከፈት የሃይል እርምጃዎችን ቢወስዱም በህብረተሰቡ ተቀባይነት ሊያገኙ ግን አልቻሉም። በወለጋ ለቀምት ከተማ አድማውን ተከትሎ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የመመገብ ግብረሰናይ ስራዎች በከተማው ወጣቶች አስተባባሪነት እየተከናወኑ ነው።
በሱልልታ የንግድ ቤቶችን በግዳጅ ለማስከፈት መስተዳድሩ ወረቀቶችን በመለጠፍ ማሸግ ጀምሯል። በግዳጅ ነጋዴዎችን በማዋከብ አካላዊ ጉዳቶችን አድርሰዋል።
በቡራዩ አድማውን ተከትሎ በተለይ ሥጋ ቤቶች ንግዳቸውን አቁመው ለተከታታይ ሶስት ቀናት ዝግ ሆነው ውለዋል። ገዥው ህወሃት/ኢህአዴግ ምንም ዓይነት ሕዝባዊ እንቢተኝነት እንደሌለ ለማስመሰል የሚያደርገው ሙከራዎች ታአማኒነት አጥተዋል። የኦህዴድ ካድሬዎች ሕዝቡን ለመሰብሰብ እና አድማውን ለማስቆም የሚያደርጉት ጥረቶች ሙሉ ለሙሉ ከሽፈዋል።