በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደው ተቃውሞ መቀጠሉ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 7/2010) በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደው ተቃውሞ ቀጥሎ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ዛሬ መንገዶች ተዘግተው መዋላቸው ታወቀ።

በጫንጮ ትላንት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በከተማዋ ምንም ዕይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በፍቼ ህዝቡ ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣት የህወሀት መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ የጠየቀ ሲሆን መንገዶች በተቃጠለ ጎማ ተዘግተው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ ተገልጿል።

በየከተሞቹ በሚደረገው ሰልፍ የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ እንዲነሳም ተጠይቋል።

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ በአምቦ ሻሸመኔ የጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ሌሎች ከተሞችን ጨምሮ ቀጥሏል።

በእስከአሁኑ ተቃውሞ ከ10 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከትላንት ጀምሮ ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተቃውሞውን ተቀላቅለው የህወሀት መንግስት በአስቸኳይ እንዲወርድ የበመጠየቅ ላይ ናቸው።

ሱሉልታ፣ ጫንጮ፣ ሙከጡሪ፣ ገብረጉራቻና ፍቼ ትላንት የጀመሩትን ተቃውሞ ዛሬም የቀጠሉ ሲሆን አብዛኞቹ መንገዶች በሰልፈኞች መዘጋታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ትላንት በጫንጮ በተካሄደው ተቃውሞ በህወሀት ታጣቂዎች ሁለት ሰዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን ዛሬ ከተማዋ ጭር ብላ ውላለች።

ትምህርት ቤቶች የመንግስት መስሪያ ቤቶች የንግድ ቦታዎች ተዘግተው መዋላቸውን የአካባቢዎ ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

በፍቼ፣ ገበረጉራቻና ሙከጡሪ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ መዋሉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በፍቼ መስመር ያሉት ከተሞችና መንደሮች ህዝባዊው ተቃውሞ የተዳረሰባቸው ሲሆን የህዝብ ማመላለሺያ አውቶብሶችን ጨምሮ በርካታ ተሽከርካሪዎች ከእንቅስቃሴ ተገተው ለበርካታ ሰዓታት ቆመው እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።

ከሶስት በላይ ተሽከርካሪዎች መስታወታቸው ተሰባብሯል ያሉት በአካባቢው የነበሩ ሰዎች መንገዶች በተቃጠሉ ጎማዎች በመዘጋታቸው በመጡበት የተመለሱ ተሽከርካሪዎች እንደነበሩም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል አብዛኞቹን አካባቢዎች እያዳረሰ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ የሚነሱት ጥያቄዎች ተመሳሳይ ናቸው።

ጎልቶ በመውጣት እየተሰማ ያለው ዋና መልዕክት ግን የወያኔ አስተዳደር በቃን የሚል ነው።