በኦሮሚያ ክልል ኩምቢ ወረዳ በተከሰተ ግጭት ወደ 49 ሺህ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ተመድ ይፋ አድረገ

 

ኢሳት (ሃምሌ 26 ፥ 2008)

በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ስር በምትገኘው የኩምቢ ወረዳ በቅርቡ በተከሰተ ግጭት ወደ 49 ሺህ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ አድርጓል። Oromia

በአካባቢው በኦሮሚያ ክልል ለወራት የዘለቀው ተቃውሞ ዳግም ያገረሸ ሲሆን፣ ነዋሪዎች ከቀያቸው ሊፈናቀሉ የቻሉበትን ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥቧል።

ይሁንና፣ በርካታ ህዝብ በሚኖርበት የኩምቢ ወረዳ ለቀናት ሲካሄዱ በቆዩ ግጭቶች 49ሺ አካባቢ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለአስቸኳይ እርዳታ መጋለጣቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

የኦሮሚያ ክልል የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን እነዚሁኑ ሰዎች ለመርዳት ለብሄራዊ የአደጋ መከላከልና አመራር ኮሚሽን ጥሪን ያቀረበ ሲሆን ከቀያቸው ተፈናቅለው የሚገኙት ነዋሪዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ታውቋል።

ለወራት በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየው ተቃውሞ ሰሞኑን በምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ ዞኖች ስር በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞን ለመቆጣጠር እየወሰዱ ባለው እርምጃ በርካታ ሰዎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና ለእስር እንደተዳረጉ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።

በኩምቢ ወረዳ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ካለው እርምጃ ጋር የተገናኘ ይሁን አይሁን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን በአካባቢው ህዝባዊ ተቃውሞ በመካሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል።

በምዕራብ ሃረርጌ በምትገኘው የባዴሳ ከተማ ሰኞ በተካሄደ ተመሳሳይ ተቃውሞ ቁጥራቸው በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎች መሞታቸውንና በርካታ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውንም የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

ይኸው በኦሮሚያ ክልል በመካሄድ ላይ ያለው ተቃውሞ ወደ ሌሎች ክልሎች በመዛመት ባሳለፍነው እሁድ በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ ታላቅ ህዝባዊ ተቃውሞ መካሄዱ ይታወሳል።