ኢሳት (መጋቢት 2 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል እስርና ማንገላታቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ገለጹ።
ዶ/ር መረራ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ትናንት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በኦሮሚያ ክልል ስላለው ህዝባዊ ንቅናቄ አስመልክቶ በፓርላማ ቀርበው የተናገሩትን ንግግርም አጣጥለዋል።
አቶ ሃይለማሪያም ይቅርታ የሚመልስና ጥፋትን የማመን ዝንባሌ ያሳዩት ለፈረንጅቱ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ነው ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ኣሁንም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ህዝቡ እየተንገላታ፣ እየተገደለና እየታሰረ ነው ብለዋል።
ዶ/ር መረራ ኢህአዴግ ተቃዋሚ ናቸው ያላቸውን ሁሉ በየእስር ቤቱ አጉሮ እያሰቃያቸው እንደሆነ ለኢሳት በስልክ በሰጡት ቃለመጠይቅ አብራርተዋል።
ኢህአዴግ አጠፋሁ ቢልም ህዝብን ያንገላቱትና የገደሉትን ለፍርድ አቅርቦ አያሳይም ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ሆኖም በተቀራኒው አመጽ ሊያስነሱ ይችላሉ ብሎ የጠረጠራቸውን ሁሉ እየገደለና በገፍ እያሰረ እንደሚገኝ ለኢሳት ተናግረዋል።
ህዝቡ በመልካም አስተዳደር ተማርሮ ያቀረበውን ተገቢ ጥያቄ ነው በማለት ትናትን አቶ ሃይለማሪያም የተናገሩትን ንግግር ከፓርላማ ወሬነት ባለፈ ትርጉም አልባ እንደሆነ ዶ/ር መረራ የአቶ ሃይለማሪያምን ንግግር አጣጥለዋል።
መንግስት ሊቃወሙ ይችላሉ የተባሉ ሰላማዊ ዜጎች ኣየገደሉና እያደኑ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ግን እስካሁን ለፍርድ የቀረቡበትን ሁኔታ አለማየታቸውንም ዶ/ር መረራ ለኢሳት ተናግረዋል።