በኦሮሚያ ክልል አሁንም ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

ኢሳት (ጥር 12 ፥ 2012)

በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች ያገረሸ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቋውሞ በምዕራብና በምስራቅ የኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ ከተሞች መቀጠሉ ተገልጿል።

የሰሞኑ በመኢሶ ሲካሄድ የሰነበተው ተቃውሞ እልባት ያላገኘ ሲሆን ተመሳሳይ ተቃውሞዎችም በወለጋ አካባቢ በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የተቋረጡ የከፍተኛ ትምርት ተቋማት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ እየተደረገ ያለው ጥረትም ተማሪዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ ምክንያት አለመሳካቱ ተገልጿል።

በእስር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥያቄን እያቀረጉ ያሉት ተማሪዎቹ በትምህርት ተቋማት አካባቢ ሰፍረው የሚገኙ የፀጥታ ሃይሎች ለደህንነታቸው ስጋት እንደሆኑባቸው በመግለጽ ከስፍራው እንዲለቁ ጠይቀዋል።

ይሁንና የጸጥታ ሃይሎቹ ሁከት የሚፈጥሩ ሰዎችን ለመያዝ የተሰማሩ ናቸው በማለት የክልሉ የፖሊስ ሃላፊዎች ምላሽ መስጠታቸው ተውቋል።

ከተጀመረ 60 ቀናት ያለፈው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ከ 150 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑም በበርካታ የአለም-አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ጭምር ተገልጿል።

የፓርቲ አመራሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የፀጥታ ሃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለእስር ዳርገው እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ውሏል ቢሉም ከነዋሪዎችና ከተማሪዎች ጋር ድርድርን እያካሄዱ መሆኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።