በኦሮሚያ ክልል ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት መኖራቸው ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 18/2010)በኢትዮጵያ አሁን እየታየ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ ሕልም ያነገቡ አካላት በኦሮሚያ ክልል ችግር እየፈጠሩ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

በባሌ ጎባው ግጭት ውስጥ ከስልጣን የተወገዱ ግለሰቦችና የጸጥታ አካላትም ተሳታፊ መሆናቸው ተመልክቷል።

ከዚህ ግጭት ጋር በተያያዘ 35 ሰዎች መያዛቸውን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ገልጸዋል።

ደምቢ ዶሎ ላይ ነፍሰጡሯን ኢትዮጵያዊ ገድለዋል የተባሉ ሶስት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተመልክቷል።

የባሌ ጎባ ከተማ አስተዳደር ሃላፊዎችና የዞን አመራሮች ማስቆም የሚችሉትን ግጭት ባለማስቆማቸው በእነሱም ላይ የማጣራት ስራ መጀመሩ ይፋ ሆኗል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ዛሬ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍና በቄሮዎች ስም ሕገ ወጥ ድርጊቶች በመፈጸም ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሕዝብና በመንግስት መካከል የተፈጠረውን መቀራረብ ለመበረዝ እንቅስቃሴ ያደረጉት ሃይሎች አሁን በሃገሪቱ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ ሕልም ያነገቡ ናቸው ብለዋል።

በዚህ ሒደት ውስጥ ጥቅማቸው የተነካባቸው ፖለቲከኞችና ሕገወጥ ነጋዴዎች ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በዚህም ምክንያት ሃላፊነት የማይወሰድባቸው ጥቃቶች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ዶክተር ነገሬ ሌንጮ አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በሳምንቱ መጨረሻ በባሌ ጎባ ከደረሰው ግጭት ጋር በተያያዘ 35 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ገልጸዋል።

በባሌ ጎባ ለ11 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት በሆነው ግጭት 100 ሰዎች ያህል እንደቆሰሉም ተመልክቷል።

ግጭቱን የቀሰቀሱትና የሃይማኖትና የዘር መልክ እንዲይዝ የተንቀሳቀሱት ከመንግስት ሃላፊነት የተወገዱ ባለስልጣናትና የጸጥታ አካላት ጭምር ናቸው ብለዋል።

አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የዞንና የወረዳው አመራሮች ግጭቱን ማስቆም እየቻሉ ይህንን ባለማድረጋቸው በእነሱ ላይም የማጣራት ስራ ለማካሄድና ሕዝብን ለማወያየት በኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ አዳነች አበቤ የተመራ ልኡክ ጎባ መግባቱ ተመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ሰኞ ሐምሌ 16/2010 በደምቢዶሎ ከተማ አንዲት ነፍሰ ጡር ገድለው፣ሌሎች አራት ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታውቋል።

በባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ነፍሰጡሯን ወደ ሆስፒታል ይዘው አብረው ሲጓዙ በነበሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት ያደረሱ ሶስት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ተናግረዋል።

የደምቢ ዶሎ ከተማ ሕዝብ ድርጊቱን በማውገዝ ትላንት ማክሰኞ ትዕይንተ ሕዝብ ማካሄዱን ገልጸዋል።

ትዕይንተ ሕዝቡም በሰላም መጠናቀቁ ታውቋል።