በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሏል

ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)

ከ150 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት እንደሆነ የተነገረለት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በሳምንት መገባደጃና ሰኞ በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች መቀጠሉ ተገለጸ።

እሁድ በትንሹ ለስድስት ሰዎች መገደል መንስዔ የሆነው የመኢሶ ከተማ ተቃውሞ ሰኞ መቀጠሉንና በአካባቢው ያልተለመደ የጸጥታ ስጋት መንገሱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

በምስራቅ ወለጋ ዳግም ያገረሸው የነዋሪዎችና የተማሪዎች ተቃውሞም በጨንጊ አካባቢ የቀጠለ ሲሆን ቁጥሩ ሊታወቅ ያልቻለ ሰውም ለእስር መዳረጉን ለመረዳት ተችሏል።

በተለያዩ የክልል ከተሞች ቀጥሎ ከሚገኘው ተቃውሞ በተጨማሪም በበርካታ ዩኒቨርስቲዎች ተቋርጦ የነበረው ትምህርት አለመቀጠሉንም ተማሪዎች አስታውቀዋል።

ትምህራቸውን አቋርጠው የሚገኙ ተማሪዎች ለእስር የተዳረጉ ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁና የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን የግድያ እርምጃ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫን ያወጣው የኦሮሚያ ክልል መንግስት በበኩሉ በክልሉ ሁሉም ስፍራዎች ሙሉ መረጋጋት ተፈጥሯል ሲል ገልጿል።

ይሁንና፣ ሁለት ወርን የዘለቀው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በአምቦ ዩንቨርስቲ እንዲሁም በምዕራብ ወለጋ ባሉ አካባቢዎች ቀጥሎ እንደሚገኝ ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተቋረጡ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግም ከነዋሪዎች ጋር የሚያደርጉት ጋር የሚያደርጉትን ውይይት ቀጥለው እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።

ሂዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ቀጥሎ በሚገኘው በዚሁ ተቃውሞ በትንሹ 150 ሰዎች መገደላቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ባሳለፍነው ሳምንት አሜሪካ የፀጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለው እርምጃ እንዳሳሰባት በመግለጽ የኢትዮጵያ መንግስት ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ማሳሰቧ ይታወሳል።