ኢሳት (ጥር 6 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል ዳግሞ ቀጥሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ አርብ በምስራቅ ሃረርጌ እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሲካሄድ መዋሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችና ተማሪዎች የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለውን እርምጃ በማውገዝ የተቃውሞ መልዕክቶችን ማስተላለፋቸውን ታዉቋል።
ይሁንና የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞውን ለመበተን በወሰዱት እርምጃ በርካታ ተማሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ተመሳሳይ ተቃውሞም በምዕራብ ወለጋ አካባቢ መካሄዱን ለመረዳት ተችሏል።
የአምቦ ዩንቨርስቲን ጨምሮ በዲላና በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትምህርት ማስተማሩ ሂደት አሁንም እንደተቋረጠ ተማሪዎች አስታውቀዋል።
ዩንቨርስቲዎቹ ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማሳሰቢያ ቢያወጡም ትምህርት አለመጀመሩን ተማሪዎች አክለው ገልጸዋል።
ትምህርታቸውን አቋርጠው የሚገኙ ተማሪዎች ለእስር ተዳርገው የሚገኙ ተማሪዎች እንዲፈቱና የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን የሃይል እርምጃ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
በዩንቨርስቲዎቹ ሰፍረው የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች ለደህንነታቸው ስጋት ኣንደሆኑባቸው የሚገልጹት እነዚሁ ተማሪዎች፣ ጥያቄያቸው ምላሽ ካላገኘ ትምህርታቸውን እንደማይቀጥሉ ገልጸዋል።