ኢሳት (ታህሳስ 27 ፣ 2008)
በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ ከትናንት ጀምሮ በጭሮ (አሰበ ተፈሪ) እና በሒርና በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ እና ሃረር የሚወስዱት መንገዶች ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸው ታወቀ።
መንግስት ተቃውሞውን በጠመንጃ ሃይል ለማስቆም በወሰደው እርምጃ በርካታ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን መዘገቡ ይታወሳል። በተቃውሞው ከተሳተፉት ሰዎች ውስጥ በጥይት ተመተው ህይወታቸው አስጊ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች ቁጥር እጅግ በርካታ ናቸው ተብሏል።
ሁለት ወር ባስቆጠረው የኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ንቅናቄ ከ140 በላይ ኢትዮጵያውያን በመንግስት ወታደሮች መገደላቸው ታውቋል። የግድያው ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በወለጋ ዩንቨርስቲ የምግብ ሳይንስ አራተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ሆራ በንቲ ሰኞ ታህሳስ 25 2008 ከሚማርበት ግቢ በመንግስት ታጣቂዎች ረቡዕ ዕለት ተገድሎ አስከሬኑን ወንዝ ውስጥ ተጥሎ ተገኝቷል።
ተማሪ ሆራ በንቲ የኢሊባቡር ገቺ ተወላጅ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በተመሳሳይ መልኩ በትናንትናው ዕለት በምዕራብ ሃረርጌ መሰላ በነበረው ተቃውሞ የተገደለው አባስ አብዱልራህማን ረቡዕ ዕለት የቀብር ስነስርዓት ተፈጽሟል።
ከቀናት በፊት በዲላ ዩንቨርስቲ የደረሰውን አደጋ ተከትሎም በአዳማ ዩንቨርስቲ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን፣ ሁለት ተማሪዎች መገደላቸውንም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል። ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ ተማሪዎች ሁለቱ ተማሪዎች በፌደራል ፖሊስ መገደላቸውንና ድርጊቱ ከፍተኛ ቁጣ መቀስቀሱን ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
በዛሬው ዕለት ህዝባዊው አመጹ በደደር፣ በሰሜን ሸዋ ገብረ-ጉራቻ፣ በርሲ ኮኮሳ፣ በኢሊባቡር ዳሪሙ፣ በሰላሌ ኢጀሬ በባሌ ሮቤ ወረዳዎች ተባብሶ ቀጥሏል።
ከሁለት ቀናት በፊት በአዳማ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች በተነሳው ተቃውሞ አንድ ተማሪ ከተገደለ እና በርካቶች ከታሰሩ በኋላ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው በመውጣታቸው የመማር ማስተማር ሂደት ተቋርጧል። በሆለታ ወታደሮችና ፖሊሶች የከተማውን ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመክበብ ተማሪዎችን ሲያስፈራሩና ሲያዋክቡ መታየታቸውን እማኞች ለኢሳት ተናግረዋል።
በዲላ ዩንቨርስቲ የተፈጸመውን የእጅ ቦንብ አደጋ ተከትሎም ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ዩንቨርስቲውን ለቀው የወጡ ሲሆን በከተማም የትራስፖርት እጥረት መስተጓጎሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በዩንቨርስቲው በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ አደጋ አራት ተማሪዎች መሞታቸው ቢገለጽም መንግስት በበኩሉ ሁለት ተማሪዎች መሞታቸውን አረጋግጧል።
ይሁንና አደጋው በማን እንደተፈጸመ ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ ነው ሲል ፖሊስ ረቡዕ በድጋሚ አስታውቋል።
ለደህንነታቸው ስጋት እንዳደረባቸው የሚናገሩት ተማሪዎች በበኩላቸው ከአደጋው በተገናኘ ተጠርጣሪ ናቸው የተባሉ ተማሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
ከመጋቢት 2006 ጀምሮ የአዲስ አበባ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃውም የተጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ በወቅቱ ከ70 በላይ ኢትዮጵያውያን የተገደሉበትና በርካቶችን የታሰሩበት እንደነበር ይታወሳል።
በህዳር ወር የተጀመረው የመሬት ቅርምት ተቃውሞ ከእንደገና ዳግሞ አገርሽቶ መላው ኦሮሚያ ክልልን አነቃንቋል። ለዚህ ንቅናቄ አፋጣኝና ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት ያልሞከረው መንግስት ከ18 ወራት በፊት በአምቦ የወሰደውን የሃይል እርምጃ ዳግም ገፍቶበታል።
የኢህአዴግ ባለስልጣናት ተቃውሞውን የፀረ-ሰላም ሃይሎች የሆኑት አርበኞች ግንቦት 7ና ኦነግ ናቸው ያነሳሱት በማለት የሃይል እርምጃ እንደሚወስዱ በገለጹት መሰረት አስተባባሪና ተሳታፊ የተባሉ ከ5000 የሚበልጡ ሰላማዊ ዜጎችን ሲያስሩ የጸጥታ ሃይሎች ደግሞ ከ 140 በላይ ሰዎችን ገድለዋል።
ለህዝቡ ስለማስተር ፕላኑ በቂ ማብራሪያ ባለመሰጠቱ የተፈጠረ ችግር ነው በሚል በየከተማው የግዳጅ ስብሰባዎች ተደርጎ የነበረ ሲሆን ስብሰባዎቹ መፍትሄ ባለማምጣታቸው ማስተር ፕላኑ ህዝቡ ካልፈለገው ይቀራል የሚሉ መግለጫዎች በመንግስት ተሰጥተው ነበር። ሆኖም እነዚህ ስብሰባዎችና መግለጫዎች ህዝባዊ አመጹን ሊያስቆሙት አልቻሉም። እስር፣ ግድያ፣ እንግልት በየቀኑ በህዝቡ ላይ ኣየተፈጸመ ይገኛል።
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ የተቀሰቀሰውን ግጭት መንግስት በቁጥጥር ስር ውሏል ቢልም ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ ተቃውሞ በምዕራብና ምስራቅ ሃረርጌ አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ መቀጠሉን ለመረዳት ተችሏል። መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የኖርዌይ ኤምባሲ፣ ዜጎቹ ወደክልሉ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በድጋሚ ማሳሰቡም ይታወሳል።