በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋር ግንኙነት አላችሁ የተባሉ 20 ሰዎች ክስ ተመሰረተባቸው

ኢሳት (ሚያዚያ 14 ፥ 2008)

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ ከነበረው ተቃውሞ ጋር ግንኙነት አላችሁ የተባሉ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራርን ጨምሮ ከ20 በላይ ሰዎች አርብ የስብርተኛ ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።

ክሱን የመሰረተው የፌዴራሉ አቃቢ ህግ የፓርቲው አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ እና 22 ግለሰቦች ሁከት እንዲባባስ በማድረግ ለንጹሃን ሰዎች ሞት ምክንያት ሆነዋል ሲል በክሱ አመልክቷል።

የፓርቲው አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸው ከአራት አመት እስር በኋላ ከወራት በፊት ከእስር መለቀቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በሽብርተኛ ክስ ሲከሰሱ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።

የሽብርተኛ ክስ የቀረበባቸው 22ቱ ተከሳሾች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አባላት ናቸሁ የሚል ክስም እንደቀረበባቸው ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

አርብ ክስ ከተመሰረተባቸው ተከሳሾች ጋር አንድ ኬንያዊም የሚገኝ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ተማሪዎች እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንደሆነም ታውቋል።

በተከሳሾቹ ላይ የተመሰረተው ክስ በችሎት በተነበበ ጊዜም የተከሳሽ ጠበቆች አለመገኘታቸውንና ከተከሳሾች መካከል ስድስቱ በአማርኛ የቀረበውን ክስ እንዳልተረዱት ለችሎቱ ገልጸዋል።

ለሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮን የሰጠው ፍርድ ቤትም ለስድስቱ ተከሳሾች አስተርጓሚ እንዲቀርብላቸው ጠይቋል።

የክሱን መመስረት ተከትሎም ፍርድ ቤቱ በማዕከላዊ የምርመራ እስር ቤት የሚገኙ ተከሳሾች ወደ ቃሊቲ እስር ቤት እንዲዛወሩ ትዕዛዝን ሰጥቷል።

ከወራት በፊት በድጋሚ ለእስር የተዳረጉት አቶ በቀለ ገርባ በእስር ቤት እየደረሰባቸውን ያለን ኢሰብዓዊ ድርጊት በመቃወም የረሃብ አድማ ላይ መሰንበታቸው ይታወሳል።

ለአምስት ወር በቆየው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን የፓርቲ አመራሮችና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቸ ተቋማት ሲገልጹ ቢቆዩም መንግስት ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን ቁጥር ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።

ከዚሁ ከኦሮሚያ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ 400 ያህል ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው እየተገለጸ ሲሆን፣ የአውሮፓ ህበረትና የተለያዩ ሃገራት ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡም በመጠየቅ ላይ ናቸው።