በኦሮሚያ ክልል መንግስት በሚወስደው እርምጃ ህዝቡ በፍርሃትና በጭንቀት ውስጥ መሆኑን ኤኤፍፒ ዘገበ

ኢሳት (የካቲት 17, 2008)

በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ዳግም ባገረሸባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች የፀጥታ ሃይሎች በሚወስዱት እርምጃ በፍርሃትና በጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ሃሙስ ዘገበ።

ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት የጊንጪ ከተማ ነዋሪዎች፣ የጸጥታ ሃይሎች በቀንና በምሽት ፍተሻን በማካሄድ ነዋሪዎች ላይ ስጋትን ፈጥረው እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ህይወታችን ትርጉም አልባ ሆኖብናል ሲሉ የገለጹት አንዲት በ40ዎቹ እድሜ ውስጥ የሚገኙ የሁለት ልጆች እናት፣ ለልጆቻቸው ደህንነት በመስጋት በእንቅልፍ እጦት እንደተሰቃዩ አስታውቀዋል።

በከተማዋ ዙሪያ የጸጥታ ሃይሎች ተሰማርተው እንደሚገኙ የሚናገሩት የጊንጪ ከተማ ነዋሪዎች በምሽት ለተለያዩ ጉዳዮች የሚንቀሳቀሱ ሰዎች በመታሰር ላይ እንደሆኑም አክለው ግልጸዋል።

የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ ሃይሎች መታወቂያን እና የግል ስልኮችን በመበርበር በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ፍርሃትንና ጭንቀትን አስረድተው እንደሚገኙ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እማኞችn ዋቢ በማድረግ በዘገባው አስነብቧል።

ይኸው ችግር ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው አምቦ ተመሳሳይ መሆኑን ያወሳው የዜና አውታሩ ነዋሪዎች በጸጥታ ሃይሎች እየደረሰባቸው ያለን የሃይል እርምጃ ዘርዝሯል።

በከተማዋ ሰፍረው የሚገኙ ወታደሮች በቋንቋ እንኳን ከህብረተሰቡ ጋር እንደማይግባቡ የሚናገሩት ነዋሪዎች የታጠቁት መሳሪያ ብቸና ቋንቋቸው ነው ሲሉም አክለው ገልጸዋል።

ሶስተኛ ወሩን አስቆጥሩ የሚገኘው ይኸው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ለበርካታ ሰዎች ሞትና እስራት ምክንያት ሆኖ መቀጠሉን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል።

የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞ በጥፋት ሃይሎች የተቀነባበረ ነው በማለት የሃይል እርምጃን እንደሚወስዱ ቢገልጹም በርካታ ነዋሪዎች መብታቸውን ለማስከበር እንደሚቀጥሉ ለዜና አውታሩ አስታውቀዋል።

በተያዘው ሳምንት ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው ሂውማን ራይትስ ዎች በተቃውሞው ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና የሃይል እርምጃውም ተጠናክሮ መቀጠሉን መግለፁ ይታወሳል።