(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 7/2009) በኦሮሚያ ከቀን ገቢ ግምት ጋር ተያይዞ ነጋዴዎች ከሚያነሱት ጥያቄ ዘጠና በመቶው ከግንዛቤ እጥረት የተያያዘ መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ዋና ዴሬክተር ገለፁ።
የክልሉ ገቢዎች ዋና ዴሬክተር አቶ አህመድ ቱሳ እንደገለፁት ከጥያቄዎቹ መካከል ሊታይ የሚገባው 10 በመቶ ብቻ ነው።
የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ቱሳ በጽ/ቤታቸው ለመንግስት፣ የድርጅትና የግል የሚዲያ ተቋማት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኦሮሚያ የግብር ግመታውን ውጤት ለነጋዴው ከመግለፁ በፊት አስቀድሞ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በኦሮሚያ በሚገኙ በሁሉም ከተሞች የግብር ትመናው ውጤት ከመገለፁ በፊትና በኋላ ከነጋዴዎች ጋር ውይይት በማድረግ እያንዳንዱ ግብር ከፋይ የርሱን ድርሻ እንዲጫወት ተደርጎ መተማመን ተደርሷል በማለት ተናግረዋል። ይህም ክልሉ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ የሰራው ነው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በተገለፀው የገቢ ግምት ውጤት ላይ ቅሬታ ያቀረቡ ነጋዴዎች መኖራቸውን አምነዋል። ከቀረቡት ቅሬታዎች ውስጥ እስከ ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ከግንዛቤ እጥረት ጋር የተያያዘ እንደሆነ፤ እንዲሁም አስር በመቶ ያህሉ ቅሬታ በሚያቀርቡት ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ ሊታይላቸው የሚገባ መሆኑን አሳውቀዋል።
በኦሮሚያ ከቁርጥ ግብር ግመታ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተቃውሞና ቅሬታ ከመቅረቡ ባሻገር በተወሰኑ አካባቢዎች የሕዝብ አመፅና ቁጣ በአደባባይ ተከስቷል።
በተለይም በአምቦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ሕዝቡ አደባባይ በመውጣት የፌደራል ፖሊስ መኪኖችን አቃጥሏል ተብሏል። በአዳማም በተመሳሳይ የሕዝብ ቁጣ መኖሩ ተነግሯል። በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሳው ተቃውሞ እንደገና እያገረሸ መሆኑንም ዘገባዎች አመልክተዋል።