በኦሮሚያ ባለስልጣናትን የማሰር ርምጃ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 30/2010) በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ላይ ኮማንድ ፖስቱ የጀመረው ዘመቻ መቀጠሉና ወደ ዝቅተኛ ካድሬዎችም መሸጋገሩ ታወቀ።

በሳምንቱ መጨረሻ በቁጥጥር ስር የዋሉት የምስራቅ ሃረርጌ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ጀማል አመዴ የሃማሬሳውን የመከላከያ ሰራዊት ጥቃት በማጋለጥ ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የተናገሩ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

የክልል፣የዞንና የወረዳ ባለስልጣናትን እንዲሁም በተዋረድ ያሉ ሃላፊዎችን ሙሉ በሙሉ ለማግለል የሚንቀሳቀሰውና በሕወሃት ጄኔራሎች የሚታዘዘው ወታደራዊ እዝ ከመካከለኛ ባለስልጣናት የጀመረውን ምንጠራ ወደ ወረዳና ቀበሌ ዝቅ በማድረግ አፈሳ በሚባል ደረጃ እስራቱ መቀጠሉም ታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባላት ያልሆኑና ያለመከሰስ መብት ያላቸውን ተመራጮች ጨምሮ በማሰር ላይ የሚገኘው በሕወሃት ሰዎች የሚመራው ኮማንድ ፖስት የዞን አስተዳዳሪዎችን እንዲሁም የከተማ ከንቲባዎችን አስቀድሞ በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል።

እስካሁን ከታሰሩት ውስጥ የምስራቅ ሃረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አመዴ ይገኙበታል።

አቶ ጀማል አመዴ በሃማሬሳ መጠለያ ጣቢያ በተፈናቃዮች ላይ የመከላከያ ሰራዊቱ ግድያ መፈጸሙን ያጋለጡ መሆናቸውም ታውቋል።

አቶ ጀማል አመዴ በወቅቱ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ “ከአዲስ አበባ ወደ ሶማሌ ክልል እየተጓዘ ያለ ተሳቢ መኪና እንዲፈተሽ በክልሉ ፖሊሶችና በወጣቶች ጥያቄ ሲቀርብ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ የመከላከያ ሃይል የእሩምታ ተኩስ ከፈተ”በማለት አጋልጠው ነበር።

በጥቃቱም 4 ተፈናቃዮች ሲገደሉ አስራ አንድ ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ተከትሎ ኮማንድ ፖስቱ አቶ ጀማል አመዴን ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።

ከታሰሩት ባለስልጣናት ውስጥ የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ፣የነቀምት ከተማ ከንቲባና ምክትላቸው እንዲሁም የምዕራብ ወለጋ ዞን ቄለም ወረዳ የፍትህና የአስተዳደር ሃላፊው እንደሚገኙበትም ታውቋል።