በኦሮሚያ በማስተር ፕላን አማካኝነት የተነሳው ተቃውሞ በድጋሚ ማገርሸቱ ታወቀ

ኢሳት (ጥር 19 ፥ 2008)

ከማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ከሳምንት በፊት በምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ የተቀሰቀሰው ዳግም ተቃውሞ መቀጠሉ ተገልጿል።

በአካባቢው የሚኖሩ ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለውን ግድያና የጅምላ እስራት በማውገዝ ሃሙስ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ተመሳሳይ ተቃውሞዎችም በሰሜን ሸዋ አካባቢ በሚገኙ ከተሞች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ፓርላማ በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ያለውን ግድያና እስራት በማውገዝ የአውሮፓ ህብረት እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለውን የውሳኔ ሃሳብ ማጽደቁ ይታወሳል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለውን ድርጊትም በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት የአውሮፓ ፓርላማ ጥያቄን አቅርቧል።

ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለውን ግድያና እስራት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ሲገልጹ መቆየታቸውም የሚታወስ ነው።