ኢሳት (የካቲት 30 ፥ 2009)
ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነው የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል የድንበር አካባቢ ግጭት የመንግስት አመራር አባላት ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ አስታወቁ።
ከአራት ወር በላይ በዘለቀው በዚሁ ግጭት እንዲቀሰቀስ ያደርጉ አመራር አባላት መለየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ መናገራቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ይሁንና አቶ ሃይለማሪያም ምን ያህል የመንግስት አመራሮች ለግጭቱ አስተዋጽዖ እንዳደረጉና በቁጥጥር ስር ይዋሉ አይዋሉ ዝርዝር መረጃን ሳይሰጡ ቀርተዋል።
በዚሁ ግጭት ሰሞኑን ልዩ ጉባዔን አካሄዶ የነበረው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት በፌዴራል መንግስት የሚደገፍ የሶማሌ ክልል ታጣቂዎች በክልሉ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በተለያዩ የኦሮሚያ ወረዳዎች በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ የመንግስት አካላት ለፍትህ እንዲቀርቡና ግጭቱ በአስቸኳይ ዕልባት እንዲያገኝ ምክር ቤቱ ጥያቄን አቅርቧል። ሁለቱ ክልሎች በሚዋሰኑበት የኦሮሚያ የድንበር አካባቢ የተቀሰቀው ግጭት ከሃብት ጋር የተያያዘ ሳይሆን በአንዳንድ አመራር አባላት ምክንያት የተፈጠረ ነው ሲሉ አቶ ሃይለማሪያም ተናግረዋል።
በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ በቦረናና ጉጂ ዞን የተወሰኑ ቦታዎች በስተቀር አብዛኞቹ በህዝብ ዉሳኔ የተከለሉ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራሮች የክልሉን ድንበር ዘልቀው ጥቃት በማድረስ ላይ ያሉ የሶማሌ ክልል ታጣቂዎች በሰው ህይወት ላይ ካደረሱት ጉዳት በተጨማሪ ድንበር የማስፋፋት እቅድ እንዳላቸው ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት እነዚሁ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል የሶማሌ ክልል ባንዲራ ሲተክሉ (ሲያውለበልቡ) እንደነበር ማስታወቁ ይታወሳል።
በቅርቡ በሁለቱ ክልሎች የደንበር አካባቢ የተቀሰቀሰውን ግጭት አስመልክቶ ሪፖርት ያወጣው የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ በሁለቱም ወገኖች ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።
ከሶማሌ ክልል ሰርገዋል የተባሉት የመንግስት ታጣቂዎች የነዋሪዎችን ንብረት ከመዝረፍ ባለፈው ቁጥራቸው በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ነዋሪዎችን አፍነው እንደወሰዱም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በሪፖርቱ አስፍሯል። ከአራት ወር በላይ በዘለቀው ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ስለደረሰው ጉዳት የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስት እስካሁን ድረስ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።
ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በአካባቢው መረጋጋት መኖሩን ቢገልጹም ነዋሪዎች እንዲሁም የፓርቲ አመራሮች ግጭቱ ቀጥሎ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።