ኢሳት (ነሃሴ 4, 2008)
በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ዳግም ተቀስቅሶ የሚገኘው ህዝባዊ ተቃውሞ መቀጣጠሉንና የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆናቸው ተገለጸ።
ለእስር የተዳረጉ ነዋሪዎች ከእስር እንዲፈቱና በአከባቢው የተሰማሩ የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን የሃይል እርምጃ እንዲያቆሙ በመጠየቅ ላይ ያሉ ነዋሪዎች ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉን በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በአካባቢው በሳምንቱ መገባደጃ የተከናወኑ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተከትሎ በርካታ ሰዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ ነዋሪዎችም በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ታውቋል።
በሳምንቱ መገባደጃ በኦሮሚያ ክልል ተካሄዶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ በርካታ ሰዎች በዚሁ በምስራቁ ሃረርጌ ዞን ስር በምገኙ በርካታ ወረዳዎች መገደላቸውን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
የሃረሪ ክልል ፍትህና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ጀማል አህመዴ በክልሉ ድሪ ጠያራ ወረዳ በሚገኙ ሶስት አካባቢዎች ቅዳሜና እሁድ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና ሃላፊው ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ስሆን፣ ጉዳዩ ወደህግ አካል መመራቱን አክለው ተናግረዋል።
የምስራቅ ሃረርጌ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በበኩሉ በዞኑ ሰባት ወረዳዎች የተካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የኮምቦልቻ ወረዳን ጨምሮ በዞኑ ስር በሚገኙት የቀርሳ፣ ፈዲስና ሜታ ወረዳዎች ህዝባዊ ተቃውሞዎች በመካሄድ ላይ ሲሆኑ የጸጥታ ሃይሎች ድርጊቱን ለመቆጣጠር እርምጃን እየወሰዱ እንደሆነ ከሃኢገር ቤት ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።