ኢሳት (ነሃሴ 24 ፥ 2008)
የኢህአዴግ ም/ቤት ያደረገውን የ15 አመት ግምገማ ተከትሎ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ “በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከተነሱት ግጭቶች ጀርባ የውጭ ሃይል አለበት” በማለት ውንጀላ አሰሙ።
በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ በአገሪቱ የሚስተዋሉትን ግጭቶች በማባባስ ጀርባ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን እንዳትጠቀም የሚፈልጉ አገራት አሉ በማለት ተናግረዋል። አያይዘውም፣ “ሁከቶችን በገንዘብ እየደገፉ የሚገኙት እነዚህ የውጭ አገራት ለጽንፈኛ ዳያስፖራዎች ገንዘብ በገፍ እየረጩ መሆናቸውን መንስግስታቸው ተጨባጭ መረጃ እንዳለው አስታውቀዋል።
በአቶ ሃይለማሪያም ደሳኝ ንግግር ላይ ለኢሳት አስተያየታቸውን የሰጡ የዲፕሎማቲክ ሙያተኞች እንደገለጹት ከሆነ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በቀጥታ የሚያያዘው ከግብፅና ሱዳን የመሳሰሉ አገሮች ጋር ነው። ለዚህም እማኝ አድርገው ያቀረቡት ሰሞኑን በአሜሪካን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማት በኢንባሲው ድጋፍ በሚደረግላቸው ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ግብፅ እጇ እንዳለበት በግላጭ ተናግረዋል።
አቶ ሃይለማሪያም ተጨባጭ ማስረጃ አለን ካሉ ለምን ተጠያቂው ነኝ ከሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ አያደርጉም የሚሉት አስተየየት ሰጪዎች ይልቁንስ ችግሩን የራስ አድርጎ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚበጅ ምክራቸውን ለግሰዋል።
አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ በተያዘው ፓርላማ ቀርበው በአገሪቱ የታዩት ችግሮች በተለይም በኦሮሚያ ክልል የተወሰደው እርምጃ መንግስት በማንም ሳያሳብብ ሃላፊነቱን በመውሰድ ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቃል ማለታቸው የሚታወስ ነው።